አሜሪካ የየመኑን ሃውቲ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ማውደሟን ገለጸች
ሃውቲዎች ሁለት የአሜሪካ መርከቦችን መምታታቸውን ባሳወቁ ማግስት አሜሪካ የቡድኑን ይዞታዎች ደብድባለች
አሜሪካ መርከቦቿ በሃውቲዎች ስለመመታታቸው በይፋ ማረጋገጫ አልሰጠችም
አሜሪካ በየመን የሃውቲ ቡድን ይዞታዎችን መደብደቧን አስታወቀች።
ቡድኑ በትናንትናው እለት በኤደን ባህረሰላጤ ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦችን መምታቱን መግለጹ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ እዝ (ሴንትኮም) የአጻፋ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
በተፈጸመው የአየር ድብደባ ሁለት የሃውቲ ድሮኖች፣ ሶስት ጸረ ሚሳኤል ክሩዝ ሚሳኤሎች እና የመቆጣጠሪያ ጣቢያው መውደማቸውን ነው ማዕከላዊ እዙ የገለጸው።
የሃውቲዎችን ጥቃት “ሃላፊነት የጎደለውና አደገኛ ነው” መሆኑን በመጥቀስም ለቀጠናው መረጋጋት ሲባል የቡድኑን ይዞታዎች መደብደቡን እንደሚቀጥልም ጠቁሟል።
ማዕከላዊ እዙ የየመኑ ቡድን በሁለት የጦር መርከቦቹ ላይ ጥቃት ስለማድረሱ ግን ማረጋገጫ አልሰጠም።
የሃውቲ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ግን የቡድኑ አየርሃይል ድሮኖችን በማስወንጨፍ “ኮል” የተሰኘችውን የአሜሪካ የጦር መርከብን መምታቱን ገልጸዋል።
“ላቦን” የተባለችው የጦር መርከብ ደግሞ በባለስቲክ ሚሳኤል መምታቷን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሃውቲዎች በቅርቡ በሰሜናዊ የመን ሳዳ ግዛት ተመቶ የወደቀውን ግዙፍ ሰው አልባ አውሮፕላን ስብርባሪዎች የሚያሳይ ምስል መልቀቃቸው ይታወሳል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ያሳየው ቡድኑ፥ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሱን እንደሚቀጥል ገልጿል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በቴል አቪቭ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እስራኤል የሁዴይዳ ወደብ አቅራቢያን ደብድባ ስድስት ሰዎች መሞታቸውና ከ80 በላይ መቁሰላቸው ይታወሳል።
ከሆዴይዳ ጥቃት በኋላ የሃውቲዎች የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት ቀዝቀዝ ማለቱ ተዘግቧል።