በማርበርግ ቫይረስ የተጠቃ ሰው 88 በመቶ የመሞት እድል አለው
የዓለም ጤና ድርጅት በጊኒ በማርበርግ ቫይረስ ከሞተው ሰው ጋር ንኪኪ አላቸው የተባሉ አራት ሰዎች ለየ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጊኒ ማርበርግ በተሰኘው ገዳይ ቫይረስ የተጠቃ አንድ ሰው ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከጊኒ መንግስት ጋር በመተባበር በዚህ ቫይረስ ተጠቅቶ ህይወቱ ካለፈ ሰው ጋር ቀጥታ ንኪኪ አላቸው የተባሉ ሰዎችን በመለየት ላይ መሆኑን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ማርበርግ የተሰኘው ገዳይ ቫይረስ ከኢቦላ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ የህመም ምልክቶች የሚያሳይ ሲሆን ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ መዛል እና ደም በአይን እና በጆሮ መፍሰስ በበሽታው የተጠቃ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል።
በማርበርግ ቫይረስ የተጠቃ ሰው 88 በመቶ የመሞት እድል ያለው ሲሆን አጋዥ ህክምና ከተሰጠው ግን የመዳን እድል እንዳለው ድርጅቱ ገልጿል።
እስካሁን በጊኒ በተሰራው የመለየት ስራ አራት ሰዎች ተለይተው በቫይረሱ መጠቃታቸውን ወይም አለመጠቃታቸውን ለማወቅ ናሙና በጤና ባለሙያዎች ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ዘገባው አክሏል።
ከዝንጀሮ ወይም ዝንጀሮ የነካውን ፍራፍሬ ሰው ሲነካው ወይም ሲመገበው ወደ ሰዎች እንደሚተላለፍ የሚታወቀው ማርበርግ ቫይረስ ከዚህ በፊት በአንጎላ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዩጋንዳ ተከስቶ ነበር።
በማርበርግ ቫይረስ ለተጠቃ ሰው እስካሁን ቀጥታ ፈዋሽ መድሃኒት ያልተገኘ ሲሆን በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በፈሳሽ እጥረት ህይወቱ እንዳያልፍ እና ሌሎች አጋዥ ድጋፎችን በማድረግ ተጠቂዎችን በህይወት ለማትረፍ ህክምና መስጠት እንደሚቻል ተገልጿል።
ኢቦላ ቫይረስ ከሰባት ዓመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገራት በላይቤሪያ እና ሴራሊዮን ተከስቶ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።