የበሽር አላሳድ አገዛዝን ከጣሉት ዋናው የሚባለው አቡ ሙሃመድ አል ጎላኒ ማን ነው?
አሜሪካ አቡ ሙሃመድ አል ጎላኒን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል ገልጻ ነበር

በደማስቆ የተወለደው ይህ ሰው ላለፉት 24 ዓመታት በኢራቅ እና ሶሪያ በተደረጉ ውጊያዎች ላይ ሲሳተፍ ቆይቷል
የበሽር አላሳድ አገዛዝን ከጣሉት ዋናው የሚባለው አቡ ሙሃመድ አል ጎላኒ ማን ነው?
የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር የሆነችው ሶሪያ አለመረጋጋት ከተከሰተባት ከ12 ዓመታት በላይ ሆኗታል፡፡
የበርካታ ማህበረሰቦች መገኛ የሆነችው ሶሪያ በእርስር በርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየች ሲሆን ከአምስት በላይ የሚሆኑ አማጺያን የፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ መንግስትን ለመጣል ለዓመታት ሲዋጉ ቆይተዋል፡፡
ዛሬ ማለዳ ጀምሮ አማጺያን የሶሪያ መዲና የሆነችው ደማስቆን የተቆጣጠሩ ሲሆን የፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ መንግስት ማብቃቱንም አውጀዋል፡፡
ደማስቆን ጨምሮ በርካታ የሶሪያ ዋና ዋና ከተሞች ከተቆጣጠሩት መካከል ሀያት ታህሪር አል-ሻም ዌም በምህጻረ ቃሉ ኤችቲኤስ በመባል የሚታወቀው ቡድን ዋነኛው ነው፡፡
የዚህ አማጺ ቡድን መሪ ደግሞ አቡ ሙሃመድ አል ጎላኒ ይባላል፡፡ ይህ ግለሰብ በሀገሪቱ መዲና ደማስቆ እንደተወለደ ሲገለጽ አሜሪካ ኢራቅን በወረረችበት ወቅት ከኢራቃዊያን ጎን ለመሆን ወደ ባግዳድ አምርቷል፡፡
በኢራቅ እያለም በአሜሪካ ጦር ተይዞ ለአምስት ዓመታት በእስር የቆየ ሲሆን ከእስር ከተለቀቀ በኋላም ወደ ሀገሩ ሶሪያ በመምጣት አልኑስራ ጦር የተሰኘ ቡድን የአልቃይዳ ክንፍ በሶሪያ መስርቶ ቆይቷል፡፡
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2016 ላይ በሽብር ወንጀል እንደምትፈልገው እና ያለበትን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል ማስታወቂያ ወጥቶበትም ነበር፡፡
አቡ ሙሃመድ አል ጎላኒ ቀስ በቀስም ራሱን ከአልቃይዳ በማግለል የበሽር አላሳድን መንግስት በማስወገድ በሶሪያ ሁሉንም ያስማማ መንግስት የመመስረት ፍላጎት እንዳለው ከሰሞኑ ለሲኤንኤን በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግሯል፡፡
የ50 ዓመት እድሜ እንዳለው የሚገመተው አቡ ሙሃመድ አል ጎላኒ ትክክለኛ ስሙ አህመድ አልሻራ የሚባል ሲሆን አል ጎላኒ የሚል ስም መጠቀም የጀመረው የአያቶቹን መገኛ ጎላን ተራሮችን ለማስታወስ እንደሆነ ተናግሯል፡፡