የብሪታኒያ ፍርድ ቤት የዊኪሊክሰ መሥራች ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ ወሰነ
አሳንጅ የአሜሪካን ሚስጢሮች እና በአፍጋኒስታንና በኢራቅ የተደረጉ ጦርነቶችን ሰነድ ይፋ በማድረግ ይታወቃል
ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ ቢሰጥ የ 175 ዓመት እስር ይጠብቀው ነበር
በለንደን ማረሚያ ቤት የሚገኘው የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ ወይስ አይሰጥ በሚለው ጉዳይ ላይ ዛሬ ብይን ተሰጠ፡፡
በአሜሪካ መንግስት በርካታ ክሶች የቀረቡበት የ49 ዓመቱ አውስትራሊያዊ ጁሊያን አሳንጅ ወደ አሜሪካ እንደሚመለስ እየተጠበቀ ነበር፡፡ አሜሪካን እና ተቋሞቿን በመሰለል ወንጀል የተጠረጠረውን የዊኪሊክስ መስራች፣ ከአሜሪካ በተጨማሪ ስዊድንም በሌላ ወንጀል ጠርጥራው ስትፈልገው ቆይታለች፡፡
ጁሊያን አሳንጅ ግን ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ ብሪታኒያ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ገብቶ ኑሮውን እዚያው እየመራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ግለሰቡ የአሜሪካን ወታደራዊ መረጃዎች በማነፍነፍና በማተም የሚታወቅ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2019 ከኢኳዶር ኤምባሲ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ አሳንጅ አሁን ላይ በደቡብ ምስራቅ ለንደን ቤልማርሽ በተሰኘ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የብሪታኒያ ፍርድ ቤት የጁሊያን አሳንጅን ለአሜሪካ ተላልፎ የመሰጠት ጉዳይ ከተመለከተ በኋላ ተላልፎ እንዳይሰጥ ወስኗል፡፡
በአሜሪካ በስለላ ወንጀል በስዊድን ደግሞ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የተጠረጠረው ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ የሚሰጥ ቢሆን የ 175 ዓመት እስር ይጠብቀው ነበር፡፡
ዊኪሊክስ በአውሮፓውያኑ 2010 አሜሪካ በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ ያደረገቻቸውን ጦርነቶች ሰነድ ይፋ በማድረግ ይታወቃል፡፡ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመተቸት የሚታወቁት ናኦም ቾምስኪ ፣ ከዚህ በኋላ በጁሊያን ላይ የከፋ ነገር ሊወሰንና ሊፈጠር እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡ ቢሆንም የብሪታኒያ ፍርድ ቤት ግን ተላልፎ እንዳይሰጥ ሲል ወስኗል፡፡
በርካታ ሰልፈኞች ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠት የለበትም በሚል በአሜሪካ የብሪታኒያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ አቅራቢያ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ነበሩ፡፡ በርካታ ደጋፊዎቹ ጁሊያን አሳንጅ ጋዜጠኛ እንጂ ሰላይ አይደለም በሚል እየተሟገቱለት ናቸው፡፡ የአሜሪካ ጦር የሚፈጽማቸውን ግፎች በማጋለጡ ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠት የለበትም የሚሉት ደጋፊዎቹ ለብሪታኒያን የተማጽኖ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዊኪሊክስ 500ሺ የሚስጢር ሰነዶችን ይፋ አድርጓል በሚል ፣ አሳንጅ በአሜሪካ መወንጀሉ የሚታወስ ሲሆን ለአሜሪካ ተላልፎ ይሰጥ አይሰጥ የሚለው ጉዳይም በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡