የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም ከታሰበው ጊዜ በላይ ሊወስድ እንደሚችል የትራምፕ አማካሪዎች ተናገሩ
ተንታኞች ሩስያ ተጨማሪ የዩክሬን ግዛትን ለመቆጣጠር የድርድሩን ሂደት መዘግየት እንደምትፈልገው ይገልጻሉ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ጦርነቱን በ24 ሰአት ውስጥ እንደሚያስቆሙ መናገራቸው ይታወሳል
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪዎች አሁን የዩክሬን ጦርነት ለመፍታት ወራት ወይም ከዚያ በላይ እንደሚፈጅ ተናገሩ፡፡
በጦርነቱ ዙርያ ከትራምፕ ጋር የተወያዩት ሁለት አማካሪዎች ግጭቱ የሚገኝበት ውስብስብ ሁኔታ እና አዲሱ መንግስት አስተዳደሩን በሚገባ እስከሚያዋቅር ድረስ ጠንካራ እርምጃዎችን ለመውሰድ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
እነዚያ ግምገማዎች ባለፈው ሳምንት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በ100 ቀናት ውስጥ ለጦርነቱ መፍትሄ ማግኘት እንደሚፈልጉ ከተናገሩት የትራምፕ የሩሲያ-ዩክሬን ልዑክ ሌተና ጄኔራል ኪት ኬሎግ አስተያየት ጋር እንደሚሰናሰል ዘገባው አክሏል፡፡
የቀድሞው በዩክሬን የአሜሪካ አምባሳደር ጆን ሄርብስት “ጦርነቱን በመጪዎቹ ወራቶች ለማስቆም ትራምፕ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ግትር አቋም ለማስቀየር ስትራቴጂ መንደፍ ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡
ያም ሆኖ ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ካስቀመጡት የ24 ሰአት ቀነ ገድብ ጋር በእጅጉ የሚራራቅ ነው ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በስልጣናቸው የመጀመሪያ ቀን በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ስምምነት እንደሚያሰፍኑ በደርዘን በሚቆጠሩ ጊዜያት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከጥቅምት ወር መገባደጃ በኋላ ግን አነጋገራቸውን ለዘብ በማድረግ ጦርነቱ በጣም በፍጥነት እንዲቋጭ እንደሚሰሩ መናገር ጀምረዋል፡፡
በተጨማሪም ተመራጩ ፕሬዝዳንት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከመድረስ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ማቆም ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል ።
ሩሲያ በቅርብ ወራት ውስጥ ከፍተኛ የጦር ሜዳ ድሎችን አስመዝግባለች ተንታኞች ፑቲን ተጨማሪ የዩክሬንን ግዛት ለመቆጣጠር የድርድሩን ሂደት መዘግየት እንደሚፈልጉት ያሳሉ፡፡
የትራምፕ አማካሪዎች በበኩላቸው የዩክሬንን የኔቶ አባልነት ውድቅ በማድረግ ጦርነቱ አሁን ባለበት እንዲቆም እና ከሩስያ ጋር የድርድር መደላድሎችን ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አብዛኞቹ ከፍተኛ የትራምፕ አማካሪዎችም ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና መስጠትን ይደግፋሉ፤ ለአብነት በአውሮፓ ወታደሮች ቁጥጥር የሚደረግበት ከወታደራዊ ነፃ የሆነ ዞን እንዲፈጠር ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የትራምፕ የዩክሬን ተወካይ ኬሎግ በዚህ ወር በኪየቭ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ያዘገዩትም ልዑኮችን ከመላክ በፊት በመሪዎች ደረጃ የንግግር መስመርን ለማጠናከር ከማለም የመነጨ ነው ተብሏል፡፡