በጊኒ በማርበርግ ቫይረስ ከሞተው ሰው ጋር ንኪኪ እንዳላቸው የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር 155 ደረሰ
በማርበርግ ቫይረስ የተጠቃ ሰው 88 በመቶ የመሞት እድል አለው
ለዚህ ገዳይ ቫይረስ እስካሁን ፈዋሽ መድሃኒት አልተገኘለትም
የዓለም ጤና ድርጅት በጊኒ በማርበርግ ቫይረስ ከሞተው ሰው ጋር ንኪኪ አላቸው በሚል የለያቸው ዜጎች ቁጥር 155 ደረሰ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጊኒ ማርበርግ በተሰኘው ገዳይ ቫይረስ የተጠቃ አንድ ሰው ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
በዓለም ጤና ድርጅት የጊኒ ቢሮ ሀላፊ ጎርጂስ ኪ ዜርቦ እንዳሉት በዚህ ቫይረስ ተጠቅቶ ህይወቱ ካለፈ ሰው ጋር ቀጥታ ንኪኪ አላቸው የተባሉ ሰዎችን በመለየት ላይ ነው።
ማርበርግ የተሰኘው ገዳይ ቫይረስ ከኢቦላ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ የህመም ምልክቶች የሚያሳይ ሲሆን ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ መዛል እና ደም በአይን እና በጆሮ መፍሰስ በበሽታው የተጠቃ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል።
በማርበርግ ቫይረስ የተጠቃ ሰው 88 በመቶ የመሞት እድል ያለው ሲሆን አጋዥ ህክምና ከተሰጠው ግን የመዳን እድል እንዳለው ድርጅቱ ገልጿል።
እስካሁን በጊኒ በተሰራው የመለየት ስራ 155 ሰዎች ተለይተው በቫይረሱ መጠቃታቸውን ወይም አለመጠቃታቸውን ለማወቅ ናሙና በጤና ባለሙያዎች ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ከዝንጀሮ ወይም ዝንጀሮ የነካውን ፍራፍሬ ሰው ሲነካው ወይም ሲመገበው ወደ ሰዎች እንደሚተላለፍ የሚታወቀው ማርበርግ ቫይረስ ከዚህ በፊት በአንጎላ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዩጋንዳ ተከስቶ ነበር።
በማርበርግ ቫይረስ ለተጠቃ ሰው እስካሁን ቀጥታ ፈዋሽ መድሃኒት ያልተገኘ ሲሆን በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በፈሳሽ እጥረት ህይወቱ እንዳያልፍ እና ሌሎች አጋዥ ድጋፎችን በማድረግ ተጠቂዎችን በህይወት ለማትረፍ ህክምና መስጠት እንደሚቻል ተገልጿል።
ኢቦላ ቫይረስ ከሰባት ዓመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገራት በላይቤሪያ እና ሴራሊዮን ተከስቶ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።