የዓለም መሪዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የየአቅማቸውን ለመለገስ ቃል ሲገቡ አሜሪካ አልተሳተፈችም
የዓለም መሪዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የየአቅማቸውን ለመለገስ ቃል ሲገቡ አሜሪካ አልተሳተፈችም
የዓለም መንግስታትና ተቋማት ለኮቪድ-19 ክትባት እና መድኃኒት ምርምር፣ ምርት እና ስርጭት የሚውል 8 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ ተስማምተዋል፡፡ ዩ.ኤስ አሜሪካ ግን ይሄን ዓለም አቀፍ ጥረት አልደግፍም በማለት ራሷን ማግለሏ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡
8 ቢሊዮን ዶላር ቃል የተገባው የአውሮፓ ህብረት እና ከህብረቱ ውጭ ያሉት ብሪታንያ፣ ኖርዌይ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ካናዳ እና ጃፓን ባዘጋጁት በቪድዮ የታገዘ ውይይት ላይ ነው፡፡ ውይይቱ ዉጤታማ እንደሆነ የገለጹት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን “ዓለም ለጋራ ጥቅም አስደናቂ አንድነት አሳይቷል“ ብለዋል፡፡
ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን
ለዘርፉ ገንዘብ ለማዋጣት ቃል ከገቡት መካከል ኖርዌይ 1 ቢሊዮን ዶላር፣ ስዊዘርላንድ 381 ሚሊዮን ዶላር፣ አውስትራሊያ 256 ፣ ኔዘርላንድ 209.5 ሚሊዮን ዶላር ይገኙበታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ዶላር ለማዋጣት ቃል ገብታ ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ደግሞ 61 ሚሊዮን ዶላር እንደምታሰባስብ ገልጻለች፡፡ ሌሎች በርካታ ሀገራትም ለቫይረሱ ምርምር የሚውል የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ለማዋጣት ቃል ገብተዋል፡፡
ከኮቪድ-19 ጋር ክፉኛ ታግለው ከቫይረሱ ያገገሙት የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን “የኮቪድ-19 ክትባት ፍለጋው የዘመናችን እጅግ አንገብጋቢው የጋራ ጥረት ጉዳይ ነው“ ብለዋል፡፡
በቫይረሱ በተያዙ እና በሞቱ ሰዎች ቁጥር በመሪነት ደረጃ ላይ የምትገኘው አሜሪካ በዚህ ጉዳይ እንደማትተባበር አስታውቃለች፡፡ ይሄም ብዙዎችን ያስገረመና ያሳዘነ ድርጊት ሆኗል፡፡ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ፣ ዋሺንግተን የዓለም ጤና ድርጅትን ላለመደገፍ በመወሰኗ እና አሁን ክትባት ለማግኘት በሚደረገው ዓለም ዓቀፍ ጥረት ባለመሳተፏ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለክትባት እና መድኃኒት ፍለጋው አንድ ቢሊዮን ዶላር ያዋጣችው ሀገር መሪ የሆኑት ሶልበርግ “ዓለም ቀውስ ውስጥ ስትሆን ይሄን መከላከል የምንችለው በጋራ ጥረጥ ነው፤ የአሜሪካ ራሷን ማግለል ግን የሚያሳዝን ውሳኔ ነው” ብለዋል፡፡
ለምርምር የሚውለውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ትናንት በተደረገው ውይይት፣ ክትባቱ ከተገኘ ለሁሉም ሀገራት መዳረስ እንዳለበት የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በአጽንኦት ተነጋግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሀሳብ ከሰነዘሩ መሪዎች አንዱ የሆኑት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ “ክትባቱ ለሀብታም ሀገራት ብቻ ሊሆን አይገባም“ ብለዋል፡፡ ሀሳቡን የደገፉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ “ክትባቱን የሚያገኘው አካል አስፈላጊው ክፍያ ተፈጽሞለት በመረጥነው ድርጅት አማካኝነት ለመላው የዓለም ህዝብ እንዲደርስ ይደረጋል“ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ሀገራት የሚያዋጡት 8 ቢሊዮን ዶላር ለክትባት ፍለጋ እና ሌሎች የኮቪድ-19 ህክምና ተግባራት የሚውል ነው፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ 3 ሚሊዮን 670 ሺ በላይ ሲደርስ ከ253 ሺ በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡