ከ10 አሜሪካዊያን አራቱ ፕሬዝዳንት ባይደን በስልጣን ላይ እያሉ ሊሞቱ ይችላሉ ብለው ያምናሉ ተብሏል
መራጮች ፕሬዝዳንት ባይደን እንደ ፕሬዝዳንት ፑቲን አይነት መሪ ጋር ፊት ለፊት መነጋገር ሊከብዳቸው እንደሚችል ስጋት አለን ብለዋል
የፕሬዝዳንት ባይደን የማስታወስ ችሎታ መቀነስ ለዶናልድ ትራምፕ ጥሩ እድል ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ሕዳር ወር ላይ እንደሚካሄድ የሚጠበቅ ሲሆን የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣል ላይ ካሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ይፎካከራሉ፡፡
የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ባይደን በተለያዩ አደባባዮች ላይ ሲወድቁ እና ንግግር ሲያደርጉም የሰሯቸው ስህተቶች የፕሬዝዳንቱ ጤና አጠራጣሪ ነው በማለት ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ሲወያዩ የቦታዎችን፣ ሀገራትን እና አመራሮችን ስም አቀያይረው ሲጠሩም በሚዲያዎች ተቀርጸዋል፡፡
የማስታወስ ችሎታየ አሪፍ ነው-ፕሬዝደንት ባይደን
እንዲሁም በህዝብ ተሰበሰበባቸው ቦታዎች እና ከአውሮፕላን ሲወርዱ እና ሲሳፈሩ በተደጋጋሚ መውደቃቸው ለተለያዩ ትችቶችም ዳርጓቸዋል፡፡
በሶት ዓመት የሚያንሱት የ79 ዓመቱ ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ጥሩ የማስታወስ ችሎታ እንዳላቸው እና የአደባባይ ላይ ሁነቶችን በንቃት ሲፈጽሙ ታይተዋል፡፡
ጄኤል ፓርትነርስ የተሰኘው የጥናት ተቋም ባደረገው ጥናት መሰረት ከ10 ተሳታፊዎች አራቱ ፕሬዝዳንት ባይደን በድጋሚ ቢመረጡ በስልጣን ላይ እያሉ ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ብለው ያምናሉ ተብሏል፡፡
ዘ ሰን ሚዲያ በዚህ ጥናት ተቋም ውስጥ ባለሙያ ከሆነችው ስካርሌት ማጓየር ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ የፕሬዝዳንት ባይደንን ጤና በመጠራጠር ምክንያት መራጮች ድምጻቸውን ለዶናልድ ትራምፕ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
በዶናልድ ትራምፕ ላይ እየቀረቡ ያሉት ክሶችም ሆን ተብለው በምርጫው ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ተብለው የተከሰቱ ናቸው ብለውም ያምናሉም ተብሏል፡፡
ከመራጮች በተወሰዱ የቅድመ ምርጫ ጥናቶች መሰረት ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ላይ አብላጫ ድምጽ እንደሚገኙ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የምርጫውን ውጤት ይወስናሉ ተብለው ከተለዩ ሰባት ግዛቶች ውስጥ ዶናልድ ትራምፕ በስድስቱ ብልጫ እንዳላቸው ይሄው ቅድመ ምርጫ ጥናት ያስረዳል፡፡