ሀገራት ወደ ጨረቃ ደቡባዊ ክፍል ለማረፍ ለምን ይሽቀዳደማሉ?
ፉክክሩ በጨረቃ ላይ ማዕድን ለማውጣትና ወደ ማርስ ሊደረጉ ለሚችሉ ተልዕኮዎች ቁልፍ ተደርጎ ይታያል
እስካሁን በጨረቃ ላይ በተሳካ ሁኔታ ያረፉት አራት ሀገራት ብቻ ናቸው
የህንድ የጠፈር ኤጀንሲ በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ዛሬ በተሳካ ሁኔታ መንኮራኩር አሳርፏል።
መንኮራኩሯ የህንድ የጠፈር ምኞቶችን ለማሳካት እና በጨረቃ ውሃ ክፍል ላይ ያለውን እውቀት ለማስፋፋት ተልዕኮ ይዛለች።
የጠፈር ኤጀንሲዎች እና የግል ኩባንያዎች ጨረቃ ላይ ለመንገስ እየተሯሯጡ ነው። ተቋማቱ በጨረቃ ማዕድን ማውጣት እና ወደ ማርስ ሊደረጉ ለሚችሉ ተልዕኮዎች ቁልፍ አድርገው ያዩታል።
ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ቻይና በጨረቃ ላይ በተሳካ ሁኔታ መንኮራኩራቸውን ያሳረፉ ሦስት ሀገራት ናቸው፤ ህንድ ዛሬ ተቀላቅላቸዋለች።
በጎርጎሮሳዊያኑ 1960ዎቹ ተመራማሪዎች ጨረቃ ላይ ውሃ ሊኖር እንደሚችል ገምተዋል።
ሆኖም የተደረጉ የናሙና ምርመራዎች ጨረቃ ደረቅ መሆኗን አመላክተዋል።
በ2008 የብራውን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች በአዲስ ቴክኖሎጂ ናሙናዎቹን ዳግም አጥንተው፤ ሃይድሮጅን አግኝተዋል።
በ2009 ደግሞ የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) በደቡባዊው የጨረቃ ጫፍ ውሃ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የውሃ በረዶ በበቂ መጠን ካለ የጨረቃ ፍለጋ የመጠጥ ውሃ ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ መሳሪያዎችንም ለማቀዝቀዝ ይረዳል ተብሏል።
እንዲሁም ወደ ማርስ ለሚደረግ ጉዞ ወይም በጨረቃ ማዕድን ለማውጣት በጨረቃ ደቡብ ክፍል ለማረፍ ውድድሩ በርትቷል።
ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሀገራት ጨረቃ ላይ ለማረፍ ያደረጓቸው ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል።
የሩስያ ሉና-25 መንኮራኩር በዚህ ሳምንት በደቡብ ዋልታ ላይ ለማረፍ ጉዞ ቢጀምርም፤ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ መከስከሱ ተነግሯል።
የተመድ የጠፈር ስምምነት የትኛውም ሀገር ጨረቃን የግሉ ማድረግን ይከለክላል።