ምክር ቤቱ የእፎይታ ጊዜን የሰጠው ለሕዝብ ደኅንነት እንጂ ለፓርቲዎች አይደለም- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
መንግስት ለውሳኔው ተግባራዊነት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም አስታውቀዋል
መጭውን ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵውያን የሚመጥን ለማድረግ በቂ ዝግጅት እያደረግን እንቆያለንም ብለዋል
ምክር ቤቱ የእፎይታ ጊዜን የሰጠው ለሕዝብ ደኅንነት እንጂ ለፓርቲዎች አይደለም- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞነኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ጋር በተያያዘ መልዕክትን አስተላለፉ፡፡
ውሳኔው ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ በር የከፈተ ሂደት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ራሱን በራሱ እያጎለበተ ለመሄድ እንደሚችል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አጋጣሚው የወቅቱን ፈተና ለማለፍ ከማገዝ ባለፈ እንደ ሀገር ዴሞክራሲን ለመለማመድ የሚያስችል ትልቅ እድልን ስለመፍጠሩም ነው በመልዕክታቸው ያስቀመጡት።
ምክር ቤቱ የእፎይታ ጊዜን የሰጠው ለሕዝብ ደኅንነት እንጂ ለፓርቲዎች አይደለም ያሉም ሲሆን መንግስት ለውሳኔው ተግባራዊነት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት እና ገዥው ፓርቲም በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተመካከረ መሥራቱን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን መጭውን ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵውያን የሚመጥን ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ተአማኒ ለማድረግ በጋራ በቂ ዝግጅት እያደረግን እንቆያለንም ነው ያሉት ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩመንግስትም አጋጣሚውን ሀገርና ሕዝብን ለማዳን ግዳጅ እንደተሰጠው አድርጎ ይቀበለዋል በሚል ያከሉም ሲሆን ገዥው ፓርቲም ተጨማሪ የሥልጣን ዘመን ሳይሆን፥ እንደ ተጨማሪ የኃላፊነት ዘመን እንደሚያየው ተናግረዋል።
ለዚህም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት እና ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር የኮሮና መከላከል ርምጃችንን በማያውክ መልኩ በመወያትና በመመካከር እንሠራለን ለተግባራዊነቱ ከወዲሁ ቆርጠን እንነሳ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።