“ሕወሓት ህዝቡን የሚጠብቀውን ኃይል በመምታት ድንበሮችን ክፍት በማድረጉ ማንኛውም ኃይል ሊገባ ይችላል” ዶ/ር ሙሉ ነጋ
በትግራይ የፊት ለፊት ውጊያ ባይኖርም አልፎ አልፎ ግጭት ያለባቸው ስፍራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል
ከአማራ ክልል ጋር ያለው አለመግባባት ለሕወሓት ወጣቱን መቀስቀሻ አጀንዳ መሆኑን ዶ/ር ሙሉ ገልጸዋል
በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው መካረር እና ውጥረት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ፈንድቶ ክልሉን ለከፍተኛ ቀውስ ዳርጓል፡፡
የትግራይ ክልልን ሲመራ የነበረው ሕወሓት በጦርነት ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ የተመሰረተው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አሁን ላይ ሦስት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ ኃላፊነቶች አራት ሲሆኑ እነርሱም፡ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ፣ የፈራረሰውን የመንግስት መዋቅር መልሶ ማደራጀት ፣ የፈራረሱ መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ ወደ ስራ ማስገባት እና በስተመጨረሻም በክልሉ ምርጫ ለማካሔድ ምቹ ሁኔታ መፍጠርእንደሆኑ የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሰላምና ፀጥታ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ለሚዲያ ተቋማት በሰጡት መግለጫ ፣ ከሰላምና ፀጥታ አንጻር በክልሉ የሚገኙ ከተሞች ወደ ሰላም እየተመለሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች መረጋጋታቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሙሉ “በማዕከላዊ ዞን ፣ በደቡባዊ ዞን እና በደቡባዊ ምስራቅ ዞን የተወሰኑ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር አብዛኛው የትግራይ አካባቢ በሀገር መከላከያ ቁጥጥር ስር ነው ያለው” ብለዋል፡፡ በክልሉ ዋናው የሕግ ማስከበር ኦፐሬሽን ተጠናቋል ካሉ በኋላ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ግን አነስተኛ ግጭቶችአሉ ነው ያሉት ዶ/ር ሙሉ ነጋ፡፡ ይሁን እንጂ የመከላከያ ሠራዊትን መቋቋም የሚችልና ፊት ለፊት ከመከላከያ ጋር የሚገጥም የተደራጀ ኃይል አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ሠራዊቱ የተበታተነውን የሕወሓት ኃይል የመለቃቀም ስራ የጊዜ ገደብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡
በአሁኑ ሰዓት 42 በመቶ ነባር የክልሉ ፖሊሶች ተመልሰው ወደ ስራ መግባታቸውንም ዶ/ር ሙሉ ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ኃይሎች የክልሉን ፖሊስ በማደራጀት ረገድ ቀዳሚውን ሚና እየተወጡ ነውም ብለዋል፡፡
የፈራረሰውን የመንግስት መዋቅር መልሶ ማደራጀት እና ፈተናዎቹ
እንደ ዶ/ር ሙሉ ገለጻ ፣ 72 በመቶ በሚሆነው የትግራይ ክልል አካባቢ (ወረዳዎች) የመንግስትን መዋቅር ማደራጀት ተችሏል፡፡ ምዕራብ ትግራይ በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ተይዞ ስለሚገኝ በአካባቢው መንግስታዊ መዋቅር ለመዘርጋት ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት እንዳልቻለም ገልጸዋል፡፡ በደቡባዊ ትግራይም እንዲሁ በአላማጣና ኮረም አምስት ወረዳዎች ላይ በተመሳሳይ ምክንያት ጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅር ማደራጀት እንዳልቻለ አንስተዋል፡፡
“ይህ የውስጥ ጉዳይ ነው” ያሉት ዶ/ር ሙሉ ይህን ችግር ለመፍታት የፌዴራል መንግስት ግልጽ አቅጣጫ እንዳስቀመጠ ነው የተናገሩት፡፡ ይኸውም የማንነት እና የወሰን ጥያቄ በሕግ አግባብ መፈታት አለበት የሚል ነው፡፡ “ሀገራዊ ህልውናን ለማረጋገጥ የሕግ ማስከበር እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ የእንደዚህ አይነት ጥያቄ መነሳት አልነበረበትም” የሚሉተ ዶ/ር ሙሉ ፣ የሁለቱ ክልሎች አለመግባባት የህዝቦችን ትስስር በማይጎዳ መልኩ ያለግጭት መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ የተቀየረ ሕገ መንግስት እና የክልሎች መዋቅር የለም” ያሉም ሲሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ነባሩን የትግራይ ክልል በሙሉ መቆጣጠር የነበረበት መከላከያ ሆኖ ሳለ የተወሰነው ክፍል በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መያዙ ሕገ-ወጥ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ይህ የሁሉም ክልሎች እና የፌዴራል መንግስት አቋም እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ችግሩን ለመፍታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከአማራ ክልል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ እንደሆነም ዶ/ር ሙሉ ገልጸዋል፡፡
“በዚህ ወቅት ከትግራይ ህዝብ ጎን ሆኖ ከማረጋጋት ይልቅ በችግሩ ላይ ችግር መጨመር ፣ ሕዝቡ ወደ ጥፋት ኃይሉ እንዲሰለፍ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ “ይህ ቶሎ ካልተፈታ የጥፋት ኃይሉ ወጣቱን መቀስቀሻ አጀንዳ ስለሚያደርገው ሰላምና መረጋጋትን በክልሉ ለማስፈን አንዱ ፈተና ነው” ሲሉም ነው የጠቀሱት፡፡
በትግራይ እና በአማራ ክልል ያለው የወሰን ጉዳይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እንዲፈናቀል እያደረገ መሆኑንም ያነሱት ዶ/ር ሙሉ ባለፉት ሦስትና አራት ቀናት ውስጥ ብቻ ከምዕራብ ትግራይ በርካታ ህዝብ በኃይል እንዲፈናቀል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በሦስት ቀናት ብቻ ከ70 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ይፋ አድርገዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ700 ሺ በላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ድርጊት የአማራን ህዝብ እና መንግስት ይወክላል ብዬ አላስብም ያሉት ዶ/ር ሙሉ ድርጊቱን ተራ ስርቆት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ “ከህግና ስርዓት ውጭ አጋጣሚውን በመጠቀም በአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ እየተደረገ ያለው ድርጊት ተገቢነት የለውም” በማለት ድርጊቱ ቶሎ መቆም እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
“በኃይል የሚደረግ ማንኛውም ድርጊት ትዝብት እና ታሪክ ከማትረፍ ውጭ መፍትሔ ሊሆን አይችልም” ብለዋል ዶ/ር ሙሉ፡፡ በመሆኑም “የፌዴራል መንግስት እና የፌዴሬሽን ም/ቤት አቋም ይዘው ቦታውን የመከላከያ ሠራዊት ተቆጣጥሮ ፣ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬያቸው መመለስ አለባቸው” ብለዋል፡፡ ችግሩ በሕግ እና ስርዓት መፈታት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ አለመግባባትን በኃይል መፍታት እንደማይቻል “የሕወሓትን ድርጊት” በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ሕወሓት የሚያሰራጫቸው የውሸት መረጃዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሌላ ፈተና መሆናቸውንም ዶ/ር ሙሉ ገልጸዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሕዝቡ ዘንድ በቶሎ ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ “በሕወሓት ሰዎች የውሸት መረጃዎች እየተሰራጩ እንደሚገኙ” የገለጹት ዶ/ር ሙሉ ከዚህ በተጨማሪም የተበተነው “የሕወሓት ኃይል እዚህም እዚያም የሚፈጥራቸው አንዳንድ ግጭቶች” ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሰራ እያደረጉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ጥገና እና ሰብዓዊ ድጋፍ
“ከግጭት እና ከጦርነት መልካም ዜና አይሰማም” ያሉት ዶ/ር ሙሉ በጦነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ለማረም የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ የመብራት ፣ የስልክ ፣ የውሃ ፣ የባንክ እና መሰል መሰረተ ልማቶች ተጠግነው በብዙ የክልሉ አካባቢዎች አገልግሎት መጀመራቸውንም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ ይህም የህዝቡ በርካታ መሰረታዊ ችግሮች እንዲቀረፉ አስችሏል ነው ያሉት ዶ/ር ሙሉ ነጋ፡፡
ከሰብዓዊ እርዳታም ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ 4.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የመጀመሪያ ዙር እርዳታ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በክልሉ እርዳታ ያስፈልገዋል ተብሎ የተለየው ህዝብ ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ሲሆን በቀጣይነት ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ የድጋፍ አቅርቦቱ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡ ከእርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የተደራሽነት ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ዶ/ር ሙሉ ይህም ከተረጂዎች ልየታ ፣ ከትራንስፖርት እና ከጸጥታ ችግሮች ጋር የተገናኘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በእርዳታ አቅርቦት ረገድ የአምበሳውን ድርሻ የሚወስደው የፌዴራል መንግስት ሲሆን እስካሁን ለመሰረተ ልማት ጥገና እና ለእርዳታ አቅርቦት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱን ተከትሎ ወደ ክልሉ በመምጣት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እየተወያዩ ለድጋፍ ስራ እንቅስቃሴ በመጀመር ላይ ይገኛሉም ብለዋል፡፡ አስቀድሞም ቢሆን በፀጥታ ጉዳይ ለደህንነታቸው በሚል እንጂ የሰብዓዊ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የመገደብ ፍላጎት እንዳልነበረም አንስተዋል፡፡
በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶችን በተመለከተ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ማካሔድ መጀመሩንም ዶ/ር ሙሉ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለማወቅም ከፌዴራል አካል ጋር በጋራ ጥናት መጀመሩን ገልጸው የዚህን ጥናት ውጤት መሠረት በማድረግ ትግራይን መልሶ ለመገንባት የመልሶ ግንባታ መርሀ ግብር እንደሚዘጋጅ አንስተዋል፡፡
ከአማራ ክልል ውጭ ሁሉም ክልሎች ፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የተለያዩ ተቋማት በአይነት እና በገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን እና አንዳንዱ ድጋፉን ገቢ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በአሁኑ ወቅት ምንም ገቢ እንደሌለው በመጠቆም የክልሉን ወጪ የፌዴራል መንግስት በመሸፈን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በውጊያው የውጭ ኃይል ተሳትፎ
ሕወሓት “የሰላም አማራጮችን አሻፈረኝ በማለት ሁሉንም የክልሉን ድንበሮች በሚጠብቀው በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ፣ የትግራይ ህዝብ ጠባቂ እንዳይኖረው” ማድረጉን ያብራሩት ዶ/ር ሙሉ “ይህ ማለት የክልሉ መንግስት የነበረው (ሕወሓት) የራሱን ህዝብ የሚጠብቀውን ኃይል በመምታት ድንበሮችን ክፍት አድርጓል ማለት ነው” ብለዋል፡፡ በመሆኑም “ማንኛውም ኃይል ሊገባ ይችላል” ካሉ በኋላ “ለዚህ ሁሉ ጦስ ምክንያቱ የሕወሓት የጥፋት ቡድን ነው” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ ነገር ግን “የገባው የውጭ ኃይል ቶሎ እንዲመለስ የፌዴራል መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው ያለው” ካሉ በኋላ የሰሜን ዕዝን መመታት ተከትሎ የፌዴራል መንግስት ውስብስብ ፈተና እንደገጠመው በመግለጽ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂው ሕወሓት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት በድጋሚ አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የውጭ ኃይል (የኤርትራ ጦር) በትግራይ ክልል በተካሔደው ውጊያ ተሳትፏል መባሉን የኢትየዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ቢያጣጥሉም አሁን አሁን አንዳንድ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የኤርትራ ጦር መሳተፉን መግለጽ ጀምረዋል፡፡