መንግስት ከህወሓት ጋር “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” መደራደርን ለምን መረጠ?
ህወሓት ለድርድር የማይቀመጥባቸው ጉዳዮች እንዳሉ በማስታወቅ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወቃል
መንግስት በሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አዘጋጀሁት ያለውን የሰላም ምክረ ሃሳብ ሰነድ ትናንት ማጽደቁን ማስታወቁ ይታወሳል
የፌዴራል መንግስቱ እና የህወሓት ድርድር ኢትዮጵያውያን በቅርበት ከሚከታተሏቸውና ከሚጠብቋቸው ቀዳሚ ሐገራዊ ጉዳዮች መካከል ከንዱ ነው።
አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተቋማት፤ በቅርበት ያሉትን ጨምሮ 'በሩቅ ያሉ ነገር ግን ለጉዳዩ የቀረቡ ኃያል ነን ባይ ሃገራት' ጭምር ሳይቀሩ አይናቸውን ሳይነቅሉ ከሚከታተሏቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
ግጭት ቆሞ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችም ተስተውለዋል።
“ሽብርተኛ” ብሎ ከፈረጀው ህወሓት ጋር “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ደጋግሞ ከመግለፅ ባሻገር ተደራዳሪ ዐብይ ኮሚቴን ከመሠየም ጀምሮ ሌሎች ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን ያስታወቀው የፌዴራሉ መንግስት ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 11 ቀን 2014 ዓ/ም በአጽንዖት አድርጌዋለሁ ያለውን ውይይት የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫው በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ስራ ለማስጀመር በአጭር ጊዜ ተኩስ ለማቆም ከሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚገባ አስቀምጧል። ከዚህ ደረጃ ላይ ያደርሳል ተብሎ የታመነበት የሰላም ምክረ ሃሳብ ሰነድ በሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴው መፅደቁም ነው በመግለጫው የተጠቆመው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፕሬስ ሴክረታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግስት ሶስት መሰረታዊ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
አቅጣጫዎቹ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ለሰላም በመደራደር ተኩስ አቁም ላይ መድረስ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችሉ ጥልቅ ፖለቲካዊ ውይይቶችን ማድረግ እና በይደር ሊቆዩ የሚችሉ ጉዳዮችን በብሔራዊ ምክክሩ እልባት መስጠት የሚሉ ናቸው፡፡
ይህ መንግስት ለሰላም ያለውን ዝግጁነት ያረጋገጠበት ሌላኛው መንገድ መሆኑን በመግለጫቸው ያነሱት ፕሬስ ሴክረታሪያቷ ቢልለኔ የሰላም አማራጮችን ለማፈላለግ አሁንም ̒ያለምንም ቅድመ ሁኔታ̓ ዝግጁ ነኝ ያለበትን ምክንያት አስቀምጠዋል፡፡
ለመሆኑ መንግስት ለምንድን ነው “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ̓” እደራደራለሁ የሚለው?
“በጦርነቱ ምክንያት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ የአፋር እና የአማራ ህዝብም የጦርነቱ ገፈት ቀማሾች ናቸው፡፡ ዘለግ ያሉ እረፍት አልባ የስቃይ ጊዜያትንም አሳልፈዋል፡፡”ብለዋል ቢልለኔ፡፡ አሁን ግን እፎይ ሊሉ የሚችሉባቸውን የሰላም ሁኔታዎች መፍጠር ይገባል ያሉት ቢልለኔ "በትግራይ ክልል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህወሓት የፖለቲካ እስረኞች ሆነው መቀጠል ስለሌለባቸው" መንግስት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ቢልለኔ መንግስት ይህን ሲያደርግ ህወሓት በአስገዳጅ ሁኔታ የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት መመልመል መቀጠሉን፣ በሰብዓዊ አቅርቦት እና በሌሎች መንገዶች ጦር መሳሪያ ማከማቸቱን፣ በህገ ወጥ መንገድ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ገንዘቦችን ማጋበሱንና ለሌሎች ንትርኮች ድጋፍ መደረጉን፣ ነዳጅን ጨምሮ ሌሎች እርዳታዎችን ለተጎዱ አካላት ከማድረስ ይልቅ ለራሱ ማከማቸቱን እና በዚሁ ሁኔታው ሰላም እያደፈረሰ እንዲቀጥል የሚረዱት የውጭ ተዋናዮች መኖራቸውን እያወቀ መሆኑን ተናግረዋል በመግለጫው፡፡
ህወሓት ለሰላም ቅንጣት ታህል ፍላጎት ባያሳይም̓ እንኳን መንግስት አሁንም ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በኋላ በያዘው የሰላም አቋም ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
ይህ ሆኖ ሳለ ግን አሁንም ቢሆን ተጠናክረው የቀጠሉ አሳሳች የፕሮፓጋንዳ ትርክቶች አሉ ብለዋል፤ ተደጋግመው የሚቀርቡ የመሰረታዊ ግልጋሎቶች ጥያቄዎችን እንደማሳያ በማንሳት፡፡ ሆኖም ጥያቄዎቹ በአንድ ጀምበር የሚመለሱ አለመሆናውን አስቀምጠዋል፡፡ መንግስት ከአሁን ቀደምም አገልግሎቶቹን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት በቅድሚያ ሊፈቱ የሚገባቸው የደህንነት እና የአስተዳደር እንዲሁም የቴክኒክ ጉዳዮች መኖራቸውን እንዳስታወቀ በመጠቆም፡፡ ይህን ለመፈጸም የሚያስችሉና የሚያሰሩ ምቹ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ "በህገወጡ ታጣቂ ቡድን ህወሓት" ምክንያት የጎደለው ይኸው ነገር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ በክልሉ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት የሚጨነቅ ከሆነ ሰበብ ከማብዛት ይልቅ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር ተደጋግሞ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ለንግግር ሊቀመጥ ይገባል ብለዋል ፕሬስ ሴክረታሪዋ፡፡
መንግስት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ይሁን በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚደረጉ ንግግሮች ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁም ብለዋል፡፡
ዛሬ ባወጣቸው መግለጫዎች በፌዴራል መንግስቱ በኩል ወደ ሁለተኛ ዙር ጦርነት ሊያስገቡ የሚችሉ ትንኮሳዎች እየተደረጉበት መሆኑን ያስታወቀው ህወሓት ከአሁን ቀደም መሰረታዊ ግልጋሎቶች ይጀመሩ የሚለውን ጨምሮ በ”ሁሉም የትግራይ ግዛቶች፣ በሕዝበ ውሳኔ፣ በትግራይ ሰራዊት፣ በተጠያቂነት እና በካሳ” ጉዳዮች ላይ ለድርድር አልቀመጥም ሲል ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡
ፌደራል መንግስት እና ህወሓት ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ዝግጅ መሆናቸውን ቢገልጹም ማን ያደራድር በሚሉው ጉዳይ እስካሁን ከስምምነት አልደረሱም፡፡