ዕለቱ አርብ ላይ ሲውል ደግሞ የበለጠ አስፈሪ እንደሚሆን ብዙዎች ያምናሉ
ፈረንጆች እንዳይገጣጠም የሚፈልጉት አርብ እና 13 ቁጥር ዛሬ ተገጣጠመ፡፡
በምዕራቡ ዓለም 13 ቁጥር የብዙ መጥፎ እድሎች ምሳሌ ሲሆን በዚህ ዕለት ከቤታቸው የማይወጡ፣ ጉዞ የማያደርጉ እና ከብዙ ነገሮቻቸው ታቅበው የሚውሉበት ዕለት ነው፡፡
ይህ ቁጥር ከአርብ ዕለት ጋር ሲገጣጠም ደግሞ የበለጠ አስፈሪ እና መጥፎ ነገሮች የሚከሰቱበት እንደሚሆንም ይታመናል፡፡
ለአብነትም ሰዎች በህይወታቸው ጠቃሚ የሚሉትን ነገር በዚህ ዕለት እንዲፈጸም ቀጠሮ አይዙም፣ በረራዎችን ያሰርዛሉ፣በሊፍት ሲጓዙ 13ኛ ወለል ላይ ከመውረድ ይልቅ ወደላይ ወይም አንድ ወለል ሲቀራቸው ይወርዳሉ ፣ ከፍቅረኞቻቸው አልያም ከወዳጆቻቸው ጋር በዚህ ቀን ለመገናኘት አይቀጣጠሩም እናም ሌሎች ጠቃሚ የሚባሉ ስራዎችንም አይሰሩም፡፡
ዩሮ ኒውስ የታሪክ ክስተቶችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ዕለቱ የተጠላው ከጥንት ዘመን ጀምሮ አያሌ መጥፎ ክስተቶች በዚህ ዕለት በመፈጸማቸው ነው፡፡
በተለይም አርብ ዕለት በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የሚመለከው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣አዳም እና ሄዋን ከገነት እንዲባረሩ ምክንያት የሆነው የተከለከለውን ፍሬ የተመገቡት ዕለት መሆኑ፣ ቃየል ወንድሙ አቤልን የገደለው አርብ ዕለት መሆኑ በዓለም ላይ ከተከሰቱ መጥፎ ነገሮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እንዲሁም በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመን የእንግሊዙን ቤኪንግሀም ቤተ መንግስትን አርብ ዕለት መደብደቧ እና ሌሎችም በዓለም ላይ ከባድ ውድመት የደረሱ ክስተቶች የተፈጸሙት አርብ ዕለት ነው መባሉ ይህ ዕለት እንዲጠላ ምክንያት ሆኗል፡፡
የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት በአውሮፕላኖች ላይ፣ ሲኒማ ወንበሮች እና ሌሎች የህዝብ መገልገያዎች ላይ 13 ቁጥርን ከመጻፍ ይቆጠባሉም ተብሏል፡፡
እንዲሁም ሴቶች ጽንስ እንዲፈጠር የሚያስችለው እንቁላል ወደ ማህጸን የሚለቁት የወር አበባ ካዩ ከ14ኛው ቀን በኋላ መሆኑ 13 ቁጥር ሲያልፍ እንደ መጥፎ እድል ማለፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎችም እንዳሉ ተገልጿል፡፡
የ13 ቁጥር የመጥፎ እድል ምልክት አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢሆንም አሁንም በዚህ ፍርሀት የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም ተብሏል፡፡
ይሁንና 12 ቁጥር የትክክለኛነት መለኪያ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ለአብነትም ሰዓት በ12 መከፋፈሉ፣ 12 ኮኮቦች መኖራቸው፣ 12 ደቀ መዛሙርት ወይም ሀዋርያዎች መኖር፣ ዓመት ለ12 ወራት መከፋፈላቸው እና ሌሎችም ይህን ቁጥር የመልካምነት እና ትክክለኛነት መለኪያ ተድርጎ ይወሰዳል፡፡