የኢፒ አበርክቶና ጥቅም በተመለከተ ባለሞያው ምን ይላል?
በኢትዮጵያ አሁናዊ የሙዚቃ ግስጋሴ ግማሽ አልበም ወይሞ ኢፒ የሚል መጠሪያ የተሰጠው የሙዚቃ ቅርጽ ለአድማጮች እየደረሰ ነው፡፡
በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢፒ የሙዚቃ አቀራረብ አዲስ አዝማሚያ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ አዲስ ሙዚቀኞች በተለምዶ ለመተዋወቂያ ለአድማጭ የሚያቀርቡት ነጠላ ዜማ በኢፒ እየተተካ ይመስላል፡፡
ከካስማሰ እስከ ዮሐና፣ ከሳሚ ዳን እስከ ዳዊት ቸርነት፣ ከብሌን ዮሴፍ እስከ ኤቢማን የመሰሉ ሙዚቀኞች ኢፒ አልበም ለቀዋል፡፡ ለምን ተመራጭ ሆነ? ኢፒ ምን ይዞ ብቅ አለ?
ደሳለኝ አበጄ (ደስ) ድምጻዊ፣ የዜማ ደራሲና አቀናባሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በቀዳሚነት ኢፒ ካወጡ ሙዚቀኞች መሀል ግንባር ቀደም ሲሆን፤ መቆያ ተባለ የኢፒ አልበም አለው፡፡ ሙሉ አልበሙ እስኪደረስ ድረስ እንደ ስሙ ለመቆያ እንዲሆን በማሰበ ኢፒው መለቀቁን ይናገራል፡፡
ደሳለኝ እንደ አዝማሚያ ኢፒ ለሙዚቀኛውም ሆነ ለአድማጩ መልካም ነገር ይዞ ብቅ ማለቱን ያነሳል፡፡ በተለይም የሚዚቃ ሀሳቦችን ለአድማጭ ለማድረስና ለመሸጥ ሁነኛ መድረክ ነው ይላል፡፡
"ሙዚቃ መስራት ቀላል አይደለም፡፡ አልበም መስራት ደግሞ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሙዚቀኛ ነጠላ ዜማ ከሚያውጣ ይልቅ ኢፒ ቢያወጣ ያለውን አቅም ያያል፣ አልበምም ለመስራት ልምምድ ያደርጋል፣ አድማጩም ጥቅም ያገኛል፡፡ ከሚወደው ሙዚቀኛ አራት፣ አምስት ሙዚቃዎችን ያገኛል፡፡ በተለይ ለአዳዲስ ሙዚቀኞች ጥሩ መንገድ ነው" በማለት ትሩፋቱን ይገልጻል፡፡
በቅርብ ዓመታት ብቅ ካሉ የዲጂታል ሙዚቃ ማደረሻ መድረኮች መሀል የሆነው የሙዚቃዊ ስራ አስፈጻሚ ሳሙኤል ሙሉጌታ፤ በሁነቶች አስገዳጅነት ሙዚቀኛውና አድማጩ ቶሎ ቶሎ መገናኘትን የግድ በማለቱ ኢፒ ለዚህ አጋዥ እየሆነ ነው ይላሉ፡፡
የሙዚቃ ቅርጹ አዳዲስ ሙዚቀኞችን ለማስተዋወቅ፣ የሙዚቃ ሀሳብን በሰፊው ለማስተላለፍና አልበም ለማውጣት ዓመታትን ከመጠበቅ ይልቅ ከአድማጭ ጋር በአጭር ጊዜ ለመገናኘት መድረክ ሆኗል፡፡
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት የሙዚቃዊ ስራ አስፈጻሚ ኢፒ ሙዚቀኞችን ከአድማጩ ጋር በቅርበት አገናኝ ሰንሰለት ሆኗል ይላሉ፡፡
"የአርቲስቱ ገጸ-ባህሪ፣ ምን አይነት ዘይቤ ነው የሚከተለው፣ ሀሳቡ ምንድ ነው? የሚለውን እንደ አድማጭ ያያሉ፡፡ ማጣጣምም ይችላሉ፡፡ አርቲስቱ መድረክ ቢሰራ እንኳ ለአንድ መድረክ የሚሆኑ ስራዎች አሉት፡፡ ከአርቲስቱ ጋር በተሻለ መንገድ መገናኘት ይቻላል" በማለት ትስስሩን ያብራራሉ፡፡
ኢፒ ሙዚቀኞች አዳዲስ ስራዎችን ጀባ እንዲሉ ምቹ ሜዳ ሆኖ መቅረቡን የሚያነሱት ስራ አስፈጻሚው፤ ለሙዚቃ አሰራጭ ኩባንያዎችም መንቀሳቀስ ሚና እያበረከተ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ለኢፒ ልዩ ስፋራ የሚሰጠውና በቅርቡ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ስራ የተቀላቀለው የሰዋሰው መልቲሚዲያ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ሀብቱ ክፍሌ፤ መድረኩ ለአዳዲስ ሙዚቀኞች ብቻ ሳይሆን ሙዚቃ ካወጡ ረጅም ጊዜ የሆናቸውና ከአድማጩ የተራራቁ ሙዚቀኞችንም እንዲቀርቡ እያደረገ ነው ይላሉ፡፡
"ጊዜ በቆየ ቁጥር እጅሽ ላይ ስራውም ያረጃል፡፡ ማርጀት የሚባለውን ነገር [ኢፒ] ሙሉ ለሙሉ ይቀርፈዋል ማለት ነው፡፡ የደረሰልሽን ነገር ታቀርቢያለሽ" ብለዋል፡፡
ኢፒ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይም አዎንታዊ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን ባለሞያዎቹ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በዋናነት የሚያነሱት አዳዲስ ሙዚቀኞች ራሳቸውንና ሙዚቃቸውን የሚሸጡበት መድረክ ከመሆን ጀምሮ አልበም ለመስራት የሚፈጀውን የጊዜ ሂደት በማሳጠር እንቅስቃሴውን ሞቅ አድርጓል፡፡
"ኢፒ የታሰበበት ስራ ነው፡፡አምስት ስራ በአንድ እይታ፣ አሬንጅመንትና የሙዚቃ ሀሳብ ማምጣት ቀላል ስራ አይደለም፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ደረጃ ያለ አርቲስት ይህን መስራት አሪፍ ነው፡፡ እኛ ሀገር አንድ አልበም ለመስራት ከሰባት እስከ 10 ዓመታትን እንጠብቃለን፡፡ ተለቅ ተለቅ ያሉት ደግሞ ከዚህ በላይም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ እነዚህ ሙዚቀኞች በየዓመቱ ተከታታይ ኢፒ ቢያወጡሉን አስበሽዋል የምናገኘውን የሙዚቃ ብዛት? ሙዚቃውን በደንብ ነው የሚያነቃቃው" በማለት ደሳለኝ አበጀ ይናገራል፡፡
የሰዋሰው የሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ሀብቱ ክፍሌ፤ ኢፒ ለሙዚቃ እድገት ጊዜንና ምቾትን በመስጠት የቆየውን "የሙዚቃ ቀመርን" በመግፋት ዘርፉ እንዲነቃቃ በር ከፍቷል ባይ ናቸው፡፡
"ሁሉንም ነገር በአንዴው እጭቅ አድርጎ መስጠት ተለምዷል፡፡ ብዙ ሰዎች ሳይፈልጉ ይሰሩ ነበር፡፡ አልበም ይህ ያስፈልገዋል፣ እንደዚህ ያስፈልገዋል እየተባለ፡፡ አሁን የሚፈልጉትንና የሚያውቁትን ብቻ ስለሚሰሩ ጥራት ይኖረዋል" ሲሉ ዘርፉ በኢፒ አዲስ ገጽ እየገለጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለአል ዐይን ሀሳባቸውን ያጋሩ የሙዚቃ ባለሞያዎች ኢፒን ለኢትዮጵያ በሚሆን መልክና ቅርጽ አስተካክለን እተጠቀምንበት ነው፤ ወደፊትም ጠንከር ብሎ ልዩነትን ማምጣት ይችላል ይላሉ፡፡
በሌላው ዓለም አፒ ማንነትን ማሳዊያ ከሆነው ከሚክስ ቴፕ ቀጥሎ የመጣና ማሟሻ፣ የአልበም ትራፊ ወይም ምራቂ አሊያም የሙዚቃ ጭብጥ ማንጸባረቂያ ነው፡፡
ርዝመቱም ከ25 ደቂቃ እንደማይሻገር ባለሞያዎቹ ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ሙዚቃ ግስጋሴ ለኢፒ የሙዚቃ ቅርጽ መለመድና ቅቡልነት መሳ ለመሳ ሆኖለታልም፡፡ የሚዚቃ አቀራረቡ ህግ አለመኖሩም ለፈጠራና ለጀማሪ ሙዚቀኞች እድልን የከፈተ ሆኗል፡፡