ዲፕሎማቷ በአሜሪካ የብሪታኒያ ኤምባሲ የንግድ እና የኢኮኖሚ ካውንስለር በመሆን ማገልገላቸው ተገልጿል
የብሪታኒያ መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀይ ባሕር አካባቢ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ መሾሙን አስታወቀ፡፡
ሳራህ ሞንትጎሜሪ የተባሉ ዲፕሎማት ናቸው ብሪታኒያ በቀጠናዎቹ ያላትን ጥቅም እንድያስከብሩ የሾመቻቸው፡፡ ዲፕሎማቷ በአሜሪካ የብሪታኒያ ኤምባሲ የንግድ እና የኢኮኖሚ ካውንስለር በመሆን አገልግለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በገልፍ ሀገራት በየመን፣ እና በኢራን የሀገራቸው ብሔራዊ ደህንነት ጸሐፊ ሆነው ማገልገላቸው ተጠቅሷል፡፡ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ የብሪታኒያ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን የተሾሙት ዲፕሎማቷ፤ በኬንያ በሚገኝ የብሪታኒያ ከፍተኛ ኮሚሽንም ሲያገለግሉ ነበር ተብሏል፡፡
በቀይ ባህር እና በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የብሪታኒያን ምላሽ የልዩ መልዕከተኛዋ ስራ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ በአፍሪካ ቀንድ ካለው የሰብዓዊ ቀውስ እስከ ገልፍ ባለው ቀጣና ብሪታኒያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ ሰው እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ ቪኪ ፎርድ፤ አዲስ የተሸሙት ዲፕሎማት ልምድ ያላቸውና የተለዩ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀይ ባሕር አካባቢ የተሾሙት አዲሷ ልዩ መልዕክተኛ ሳራህ ሞንትጎሜሪ በዚህ ወሳኝ ወቅት ለዚህ ኃላፊነት በመሾማቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በግጭት፣ባለመረጋጋትና በአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት የሰብዓዊ መቅሰፍት ላይ እንደሆነም ነው አዲሷ ልዩ መልዕተኛ ያስታወቁት፡፡