በኢትዮጵያ “የተረኝነት ፖለቲካ” ሊኖር አይገባም -ፕ/ር በየነ
መተማመን ለመፍጠር አሸናፊው ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መስራት ይኖርበታል ብለዋል ፕ/ር
ፕ/ር በየነ ቀጣይ 5 ዓመታት የብሔራዊ መግባባት ውይይት የሚደረግበትና ሕገ መንግስት የሚሻሻልበት መሆን እንዳለት ገልጸዋል
የፖለቲካ መሪና የመንግስት የሥራ ኃላፊ በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉትን ቆይታ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ፕ/ር በየነ ቀጣዮቹን አምስት ዓመታት የተመለከቱ ጉዳዮችን ያሱበት ቃለ ምልልስ ደግሞ ቀጥሎ ይቀርባል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተረኝነት የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ የአንድ ብሔር ወይም የአንድ ቡድን የበላይነትና አለቅነት ቀደም ሲል ጀምሮም እንደነበረና አሁንም እንደቀጠለ የሚገልጹ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ በአንጻሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ መንግስት ውስጥ ያሉ ሰዎች “ተረኝነት አለ” የሚለውን ሀሳብ በአሉባልታ እንጅ በተግባር እንደሌለ ነው ይገልጻሉ፡፡
የኢሶዴፓ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የተረኝነት ፖለቲካ ሊኖር እንደማይገባ ይገልጻሉ፡፡ ፕ/ሩ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ተረኝነት ካለ እሱን ማስቆምና ሳይኖርም የሚወራ ከሆነ አስተሳሰቡን ማክሰም እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ “ተረኝነት በፍጹም ሊኖር አይገባም፤እንደት ሆኖ ነው የኔ ተራ ነው ልግዛ የሚባለው? እንዴት አደርገህ ይህንን ትልቅ ሀገር ማስተዳደር ይቻላል“ የሚሉት ፕ/ር በየነ የሙስናና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሕግ የበላይነት መጥፋትና ተረኝነት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ተረኝነት “የማይመስል ርኩሰት ያለው አዙሪት ነው“ ያሉት የኢሶዴፓ ሊቀመንበር ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ሲባል ይህን ማስቆም ይገባል ብለዋል፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ህዝብ በነጻነት እንዲወስን ዕድል ከተሰጠ ተረኝነትና ሌሎች እርሳቸው “እርካሽ“ ያሏቸው አስተሳሰቦች ቦታ እንደማይኖራቸው አንስተዋል፡፡
ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት
ፕ/ር በየነ አንድ መንግስት አሸንፎ መንግስት ማቋቋም ቢችል በዚህ ሀገር የዴሞክራሲ ሽግግሩ ተጠናቋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸው ከዚህ ምርጫ በኋላ ያሉት አምስት ዓመታት የብሔራዊ አንድነት መንግስት የሚቋቋምበት መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡
አሸናፊው ፓርቲ ሌሎች ፓርቲዎችንም በመጋበዝ ለሀገር አንድነት ሊሰራ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ በቀጣይ አምስት ዓመታት ብሔራዊ አንድነት ወይም ብሔራዊ መግባባት በሰፊው ውይይት ሊካሄድበት፤ የፖለቲካ ምህዳሩም ሊደላደል፤ ሕገ መንግስቱም ሊሻሻል የሚችልበት አንዲሆን ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሕገ መንግስት መሻሻያም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሊካሄድ እንደሚገባ ፕ/ር በየነ ያነሳሉ፡፡ ልክ እርሳቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሆነው የመንግስት የሥራ ኃላፊ እንደሆኑት ሁሉ የሌሎች ፓርቲወች አባላትነ አመራችም ወደ መንግስት ኃላፊነት መጥተው ሀገር የሚገለግሉበት ዕድል እንዲፈጠርም ጠይቀዋል፡፡ መተማመን ያለበት ሁኔታ ለመፍጠር አሸናፊው ፓርቲ ከሌሎችም ፓርቲዎች ጋር ተደባልቆ ሊሰራ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡