የ18 ወር ጨቅላ ህጻን ለመሰዋት ሙከራ ያደረገችው “ሰይጣን አምላኪ” ተገደለች
ሜክሲኳዊቷ ጠንቋይ የወንድሟን የልጅ ልጅ ከተኛበት ለመስረቅ ሙከራ ስታደርግ ነው የተገደለችው

ግለሰቧ ከኤል ቻፖ የእጽ አዘዋወሪ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላት ተነግሯል
የ18 ወር ጨቅላ ህጻን ለመሰዋት ሙከራ ያደረገችው “ሰይጣን አምላኪ” ተገደለች።
የ33 አመቷ ሜክሲኳዊት የወንድሟን የልጅ ልጅ “ለሰይጣን አምልኮ” ለመስእዋት ለማቅረብ ሙከራ ስታደርግ ነው የተገደለችው።
ማሪያ ገዋዳሉፔ የተባለችው የሰይጣን አምላኪ እንደሆነች የተነገረላት ጠንቋይ የእጽ አዘዋዋሪዎች ጠባቂ ተብሎ ለሚታሰበው ሴንት ሳንታ ሙርቴ ለተባለ ሰይጣን በተለያዩ ጊዜ መስእዋቶችን እንደምታቀርብ ተደርሶበታል፡፡
ወደወንድሟ ልጅ መኖርያ ቤት በምሽት በማቅናት የ18 ወር ጨቅላ ህጻን ለመስረቅ ሙከራ ያደረገችው ማሪያ በቤዝቦል ዱላ ጭንቅላቷን ተመታ ህይወቷ አልፏል፡፡
የጨቅላው አባት የሆነው ካርሎስ ጋብሬል አክስቱ አደገኛ ከሚባሉ የእጽ አዘዋዋሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳላት በጥንቆላ ስራ ላይ የተሰማራች መሆኑን ቢያውቅም በገዛ ዘመዷ ላይ ይህን ጭካኔ ትፈጽማለች የሚል እምነት አልነበረኝም ብሏል፡፡
የተፈጠረውን አጋጣሚ ለፖሊስ ሲያስረዳ “ሌሊት ላይ ከልጄ ክፍል የለቅሶ ድምጽ ስሰማ ወደ መኝታው ሄድኩኝ ከዛም አክስቴ ልጄን አቅፋ ለመውጣት ስትሞክር ደረስኩባት በቤዝቦል ዱላ በማስፈራራት ልጄን እንድትመልስልኝ ብጠይቃትም አሻፋረኝ አለኝ አለች። በዚህም የመጨረሻውን አማራጭ ለመጠቀም ተገድጃለሁ” ብሏል፡፡
ከእርሷ ጋር ሌሎች ሁለት ሰዎች በቤት ውስጥ እንደነበሩ እና በእርሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲጥሩ ጩኸት የሰሙ ጎረቤቶች መሰባሰባቸውን ሲመለከቱ ሮጠው ማምለጣቸውን ተናግሯል፡፡
ከቴክሳስ ድንበር አቅራቢያ በምትገኝው ሁዋሬዝ ከተማ ነዋሪዋ ማሪያ ለተለያዩ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች ሰይጣናዊ የጽሎት ስርአት እና አምልኮ የምታከናውን ሲሆን፤ በአሜሪካ እስር ቤት ከሚገኝው ታዋቂው እጽ አዘዋዋሪ ከኤል ቻፖ ጉዝማን የእጽ ቡድን ጋር ጠበቅ ያለ ወዳጅነት እንደነበራት ተነግሯል፡፡
ፖሊስ የወንጀሉን መፈጸም ተከትሎ በሟቿ ማሪያ ቤት ባደረገው ፍተሻ እድሜው 22 አመት የሚገመት ወጣት አስክሬን ማግኝቱን አስታውቋል፡፡
በአሜሪካ እና በሜክሲኮ የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ የሰዎች እና እጽ አዘዋዋሪዎች በተለምዶ ሳንታ ሙርቴ የተሰኘው ሰይጣን አምላኪዎች ሲሆኑ አደገኛ ከሆኑ ጠላቶቻቸው እና ከሚያሳድዷቸው የህግ አካላት እንደሚጠብቃቸው ብርቱ እምነት አላቸው፡፡
በነዚህ እጽ አዘዋዋዋሪ መኖርያ ቤቶች ውስጥም በተለያየ ጊዜ በተደረገ ድንገተኛ የፖሊስ ብርበራ የራስ ቅልን ጨምሮ ሌሎች የሰው አካለት እንደሚገኙ ደይሊ ሜል አስነብቧል፡፡