ዛሬ በቻይናዊው ባለሃብት የገንዘብ ድጋፍ 162 ቤተ እስራኤላውያን እስራኤል ገብተዋል
እስራኤል በ‘ሮክ ኦፍ እስራኤል’ ዘመቻ 2 ሺ የፈላሻ ሙራ አባላትን ለመውሰድ አቅዳ በመስራት ላይ መሆኗ ይታወሳል
ቤተ እስራኤላውያኑ በ6ኛው ዙር ‘ሮክ ኦፍ እስራኤል’ ዘመቻ ያቀኑ ናቸው
በዘመቻ ዙር (ዘመቻ ‘ሮክ ኦፍ እስራኤል’) ወደ እስራኤል ለመጓዝ ሲጠባበቁ የነበሩ 162 ቤተ እስራኤላውያን ዛሬ ማለዳ ቤን ጉሪዮን ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ደርሰዋል፡፡
ቤተ እስራኤላውያኑ በ6ኛው የዘመቻው ዙር ነው ወደ እስራኤል ያቀኑት፡፡
ቻይናዊው ባለሃብት ፒተር ዋንግ የቤተ እስራኤላውያኑን የጉዞ ወጪ ሸፍኗል ተብሏል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የስደተኞች ሚኒስትር ፕኒና ታመነ በጉዞ ስኬታማነት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ወንድምና እህቶቻችን ቧሏቸው ቤተ እስራኤላውያን ጉዞ ስኬት በተጫወቱት የመሪነት ሚና መኩራታቸውንም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
ከተጓዦቹ መካከል 11ዱ ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው፡፡ በድምሩ 43 ልጆች በጉዞው ተካተዋል፡፡
እስራኤል በዘመቻው 2 ሺ የፈላሻ ሙራ አባላትን ለመውሰድ አቅዳ በመስራት ላይ ነች፡፡ ከነዚህም መካከል አብዛኞቹን በይፋ አጓጉዛለች፡፡
ለዚህም 109 ሚሊዬን ዶላር ገደማ ገንዘብን በጅታ ነበር የተንቀሳቀሰችው፡፡
በኢትዮጵያ 14 ሺ ገደማ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል ለመሄድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡
አብዛኞቹ እድሉን ለማግኘት ከ15 ዓመታት በላይ የጠበቁ ናቸው እንደ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ፡፡
በአሁኑ ወቅት 140 ሺ ገደማ ቤተ እስራኤላውያን በእስራኤል እንደሚኖሩ ዘገባው ያትታል፡፡
ከነዚህ ውስጥ 22 ሺ ያህሉ እ.ኤ.አ በ1984 እና በ1991 በተካሄዱት ዘመቻ ሙሴ እና ዘመቻ ሰለሞን ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ናቸው፡፡