ለወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ በሚል የተሰራጨው የ17 ሚሊዮን ብር ኩፖን የት ገባ?
ለሆስፒታሉ ግንባታ ገቢ የሚያሰባስበው ኮሚቴ እንዲዘጋ ከአምስት ዓመት በፊት ቢወሰንም እስካሁን ኮሚቴው ስራ ላይ ነው ተብሏል
ኮሚቴው ለፕሮጀክቱ በውጭ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ሳይቀር የገቢ መሰብሰቢያ ኩፖን አሰራጭቶ ነበር
ለወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ በሚል የተሰራጨው የ17 ሚሊዮን ብር ኩፖን የት ገባ?
የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ተቋማትን የበጀት ኦዲት ዋና ዋና ግኝቶችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ላይ እንዳለው ከህዝብ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ኦዲት ካደረጋቸው ስራዎች መካከል የወሎ ተርሸሪ የህክምና እና የማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ዋነኛው ነው፡፡
በተሰራው የኦዲት ሪፖረት መሰረትም ለሆስፒታሉ ግንባታ በሚል የገቢ ማሰባሰቢያ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት ሲደረግ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ለዚህም ሲባል በውጭ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች፣ ክልሎች እና ሌሎች አካባቢዎች ይሸጣል ተብሎ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ኩፖን ተሰራጭቶ እንደነበር በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ይሁንና ይህ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው የገቢ መሰብሰቢያ ኩፖን እንደጠፋ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሆስፒታሉ ገቢ አሰባበሳቢ ስራ አመራር ቦርድ በሀገር ውስጥ ከተሰበሰበው ውስጥ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወደ ባንክ ያልገባ ሲሆን ካልተሸጠ ቶምቦላ 20 ሺህ ብርን ጨምሮ በአጠቃላይ 17 ሚሊዮን ብር ጠፍቷል በሚል የእዳ ስረዛ እንደተደረገ ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
የሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አመራር ቦርድ በ2008 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ለፕሮጀክቱ ራሱን የቻለ አንድ ብሎክ ህንጻ ለመገንባት የሚውል ሀብት አፈላልጎ በመገንባት ለወሎ ዩንቨርሲቲ እንደሚያስረክብ በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ የተባለው ህንጻ አልተገነባም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ በሰላም ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ ሆኗል- ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ
የሆስፒታሉን ግንባታ እውን ለማድረግ የህዝብ ተሳትፎን ባሳተፈ መንገድ እንዲሰራ፣ በየጊዜው ጉዳዩን እየተከታተለ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በሚል ከፕሮጀክቱ ስራ አመራር ቦርድ፣ ከወሎ ዩንቨርሲቲ፣ ከህብረተሰቡ እና ከአካባቢው አስተዳድር የተውጣጣ ከ9-11 አባላት ያሉት አዲስ የጋራ አማካሪ ቦርድ እንዲቋቋም ከስምምነት ላይ ቢደረስም ስምምነቱ እስከ ዛሬ ድረስ አልተፈጸመም ተብሏል፡፡
እንዲሁም የሆስፒታሉ ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከህዘብ የተሰበሰበውን ገንዘብ እና ቁሳቁስ ኦዲት በማስደረግ ሰነዶችን ጨምሮ ለወሎ ዩንቨርሲቲ እንዲያስረክብ፣ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱም የቆይታ ጊዜው እንዲያበቃ እና እንዲዘጋ ሚያዚያ 2010 ዓ.ም ላይ ከስምምነት ላይ ቢደረስም እስከ ዛሬ ድረስ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ እንዳልተዘጋ ተገልጿል፡፡