
አንዲት እናት ዘጠኝ ወራት አርግዛ የወለደችውን የአምስት ወር ወንድ ልጅ ለመመለስ ተገዳለች
አምጠው የወለዱት እና እያጠቡት ያለው ልጅ የእርስዎ አይደለም ቢባሉ ምን ያደርጋሉ?
ክሪስቲና ሙራይ የ38 ዓመት ሴት ስትሆን ከአምስት ወር በፊት ነበር ወንድ ልጅ የወለደችው፡፡ እናት መሆን ህልሜ ነበር የምትለው ሙራይ ለዓመታት ከተዘጋጀች በኋላ የምትመኘውን እናት መሆን ችላ ነበር፡፡
ይህን ህልሟን ለማሳካት ስትልም የወንድ የዘር ፍሬ ከሚለግሱ በጎ ፈቃደኛ በተገኘ የወንድ የዘር ፍሬ በመጠቀም የራሷን እንቁላል በሳይንሳዊ መንገድ እንዲዋሃድ እና ጽንስ እንዲፈጠር ካደረገች በኋላ የልጅ እናት መሆኗ ተገልጿል፡፡
በምህጻረ ቃሉ አይቪኤፍ ወይም በሳይንሳዊ ዘዴ በቤተ ሙከራ በሚካሄደው በዚህ ልጅ የመውለድ ጥበብ አማካኝነት ልጅ መውለዷ ደስታ እንደሰጣትም ተናግራለች፡፡
ይሁንና እሷን ነጭ መሆኗ እና የወንድ የዘር ፍሬ የለገሳት ሰው ነጭ መሆኑን ተከትሎ ነጭ ልጅ ስትጠብቅ የነበረችው ሙራይ የወለደችው ልጅ ግን ጥቁር ልጅ ሆኗል ተብሏል፡፡
ዋናው ነገር እናት መሆኔ ነው በሚል እሳቤም አምጣ የወለደችውን ልጅ ልጁ ነው ብላ ተቀብላ እየኖረች እያለ ግን ጽንሱ በቤተ ሙከራ እንዲፈጠር ያደረገው ኩባንያ ያልታሰበ ስህተት መስራቱን እና ይቅርታ ሊጠይቃት ወደ ቤቷ ይመጣል፡፡
ኩባንያው ጽንሱ በቤተ ሙከራ ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ወቅት ስህተት መፈጸሙን፣ አምጣ የወለደችው ህጻን ከሌሎች ባልና ሚስት የዘር ፍሬ የተፈጠረ እንጂ የእሷ እንዳልሆነ ይነግራታል፡፡
የህጻኑ እውነተኛ ወላጆችም ህጻኑን እንደሚፈልጉት በፈቃደኝነት ካልሰጠቻቸው ጉዳዩን ወደ ህግ ሊወስዱት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነም ኩባንያው ከይቅርታ ጋር ለሙራይ ይገልጻል፡፡
በህጻኑ ላይ በተደረገው የዘረ መል ወይም ዲኤንኤን ምርመራ መሰረትም አምጣ የወለደችው እና ጡቷን ስታጠባው በእርግዝና ወቅትም ብዙ መከራን ያሳለፈችለት ልጅ የእሷ እንዳልሆነ ትረዳለች፡፡
ጉዳዩን በስምምነት ለመፍታት ያደረገችው ጥረት ልተሳካላት ሙራይም የአምስት ወራት ወንድ ልጇን ለእውነተኛ ወላጆቹ አሳልፋ ለመስጠት ተገዳለች፡፡
ኩባንያው ካሳ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ከእሷ የዘር እንቁላል የተጸነሰ ልጅ እንድትወልድ እና ዳግም የልጅ እናት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ቢነግራትም አሁንም የሌላ ሰው ልጅ ሊያስወልደኝ ይችላል በሚል ጥያቄውን ውድቅ ማድረጓን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡