ከሞተ ሰው እጅ ላይ ጣት ቆርጣ በመውሰድ ገንዘብ ስታወጣ የነበረችው ተጠርጣሪ
ፋሲል ተክለማርያም በመኖሪያ ቤቱ ተገድሎ ተገኘቷል
ግድያ የተፈጸመበት ፋሲል አውራ ጣቱም ተቆርጦ ተወስዷል
ከሞተ ሰው እጅ ላይ ጣት ቆርጣ በመውሰድ ገንዘብ ስታወጣ የነበረችው ተጠርጣሪ
ፋሲል ተክለማርያም በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ከተማ የሚኖር ዜጋ ሲሆን በቤቱ ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።
ፖሊስ ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርት መሰረት ፋሲል በሰው እጅ በተፈጸመበት ጥቃት መገደሉን የሚያሳይ ምልክቶችን አግኝቷል።
ለአብነትም በፋሲል እግሮች ላይ፣ ጭንቅላቱ እና አንገቱ አካባቢ የስለት ጥቃቶች ተገኝተዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ከአምስት ቀናት በኋላ ሞቶ የተገኘው ፋሲል በአስከሬኑ ላይ በተደረጉ ምርመራዎች አማካኝነት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ተይዘዋል።
የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ጉዳይ ግን የፋሲል አውራ ጣት ተቆርጦ መወሰዱ ሲሆን በኋላ በተደረጉ ማጣራቶች የተቆረጠውን አውራ ጣት አሻራ በመጠቀም ገንዘብ ከባንኮች ወጪ መደረጉ ነበር።
ፖሊስ ባደረገው ክትትልም የሟች ፋሲል ተክለማርያምን አውራጣት አሻራ በመጠቀም ገንዘብ ስታወጣ የነበረችው ቲፋኒ ቴይለር ግሬይ የተባለች ፍቅረኛው ነበረች።
የ53 ዓመቱ ፋሲል ግድያው የተፈጸመበት ያሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ሲሆን ከፍቅረኛው በተጨማሪ ኦድሬይ ሚለር የተባለች ተጠርጣሪም በፖሊስ ከተያዘች በኋላ የግድያ ወንጀል ክስ ተመስርቶባታል።
እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ከሆነ ተጠጣሪዎቹ ወደ ሟች ቤት ሲገቡ፣ ሲወጡ እና ፍቅረኛው የፋሲልን አውራ ጣት ተጠቅማ ገንዘብ ስታወጣ የሚያሳዩ የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎች ተገኝተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ መረጃ ለማጥፋት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችም እንደተገኙባቸው ፖሊስ በምርመራው ላይ አስታውቋል።
ሟቹ ፋሲል ተክለማርያም ከዚህ በፊት ግሬይ የተባለችው ፍቅረኛው ያለ እሱ ፈቃድ 1 ሺህ 600 ዶላር ወጪ ማድረጓን ለፖሊስ አሳውቆ ነበር ተብሏል።