በምርጫ ክልሉ የአንድ የግል እጩ ፎቶግራፍና ሰም ባለመካተቱ ምክንያት ቦርዱ ምርጫው እንዳይካሄድ አግዶ ቆይቶ ነበር
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል በሚገኙ 30 የምርጫ ጣቢያዎች የፊታችን ሀሙስ ምርጫ እንደሚደረግ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ መግለጫ እየሰጡ ሲሆን ምርጫ ባልተደረገባቸው የነገሌ ምርጫ ክልል በሚገኙ 30 የምርጫ ጣቢዎች ምርጫው የፊታችን ሃሙስ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በነገሌ ምርጫ ክልል 139 ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፤ ምርጫ የተካሄደው በ105 ጣቢያዎች እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በቀሪዎቹ ላይ ምርጫው ሃሙስ ተካሂዶ ውጤቱም ተጠቃሎ እንደሚገለጽ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል አንድ ዕጩ ፎቶግራፋቸው እና ስማቸው አለመካተቱን ለምርጫ ቦርድ በማመልከታቸው ምርጫው ታገዶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ምርጫ ግን ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ቦርዱ የግል ተወዳዳሪው ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ ምርጫው እንዳይካሄድ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ቦርዱ ምርጫው እንዳይካሄድ ያስተላለፈው ውሳኔ በተለያየ ምክንያት በመዘግየቱ ምርጫው በ105 የምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡ ነገርግን የግል ተወዳዳሪው በእርሳቸው ምክንያት ምርጫው እንዲስተጓጎል እንደማይፈልጉ ማመልከታቸውን ይታወሳል፡፡
የቦርዱ የኮሙኒኬን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ሁሉም የምርጫ ክልል ውጤቶች ወደ ማእከል መግባታቸውንም አስታውቋል፡፡
በቁጫ የምርጫ ክልል አቤቱታን በተመለከተ በምርጫ ክልሉ ላይ ከማዳመር ጋር የተያያዘ አቤቱታ ነበር ያሉት የኮሙኒኬን ኃላፊዋ አሁን ላይ ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ም/ቤት በ86 ምርጫ ጣብያዎች ሁሉም አካላት ባሉበት ቆጠራ እያካሄድን ነው ብሏል፡፡
ሶሊያና ሽመልስ ከምርጫው ቀን አንስቶ ከቆጠራ እና ድመራ ጋር በተያያዘ 31 ፓርቲዎች እንዲሁም 7 የግል ተወዳዳሪዎች በጽሁፍ፣ ስልክና ቴክስት አቤቱታ ማቅረባቸውም ተናግሯል፡፡
ወይዘሪት ሶልያና በ153 ምርጫ ክልሎች 31 ፓርቲዎች ቅሬታ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ምርጫው በተካሄደባቸው በሁሉም ክልሎች ቅሬታ የቀረቡ ሲሆን በአማራ ክልል 49 ምርጫ ክልሎች፣ በደቡብ ክልል 40 ምርጫ ክልሎች በአዲስ አበባ ሁሉም ምርጫ ክልሎች 23 ምርጫ ክልሎች እንዲሁም በአፋር ክልል በ21 ምርጫ ክልሎች በርካታ ቅሬታ የቀረቡባቸው ክልሎች ናቸው።
የፓርቲዎች አቤቱታ ተከትሎ ቦርዱ፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉን የገለጹት ሶልያና ሽመለስ ወደ 30 የሚጠጉ የህግ ባለሙያዎች ከአቤቱታ አቀራረብ ስታንዳርድና መስፈርት ጋር በተያያዘ ለፓርቲዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ቦርዱ መስፈርቶቹን ያሟሉ አቤቱታዎችን እየመረመረ መሆኑንም ጭምር፡፡
በሂደት የተደራጀው የህግ ቡድን የውሳኔ ኃሳብ እንደሚያቀርብና በዚህም ቦርዱ የውሳኔ ኃሳቦች ላይ ተንተርሶ እስከ ሀሙስ ድረስ የመጨረሻ ውሳኔዎች ያስታውቃልም ብሏል የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልል ውጤት ተጠቃሎ ወደ ማእከል ባለመድረሱ ምክንያት አጠቃላይ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል፡፡