ታምራት ቶላ እና ሲምቦ አለማየሁ የአመቱ ምርጥ አትሌቶች ሽልማት አሸነፉ
አትሌት ታምራት ቶላ ከስታዲየም ውጪ በተደረገ የሩጫ ውድድር የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማትን አሸንፏል
አትሌት ሲምቦ አለማየሁ የዓመቱ ተስፋ የተጣለባት አትሌት ሽልማትን አሸንፋለች
የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶችን በትናንትናው እለት ሸልሟል።
በሽልማት ስነ ስርዓት ላይም ሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ዘርፎች የአመቱ ምርጥ አትሌት ሸልማቶችን ማሸነፋቸው ተነግሯል።
በዚህም መሰረት የፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ድል ባለቤቱ አትሌት ታምራት ቶላ በፈረንጆቹ 2024 ስታዲየም ውጭ የዓመቱ ምርጥ የጎዳና ላይ ውድድር አትሌት ሽልማትን አሸንፏል።
አትሌት ታምራት ቶላ በአመቱ ውስጥ የኦሎምፒክ ሪከርድ በማሻሻል የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ማሸነፉ ይታወሳል።
አትሌት ታምራት ቶላበ33ኛውየፓሪስ ኦሎምፒክ 2:06:26 በሆነ ሰዓት የኦሎምፒክ ክብረ ወሰንን አሻሽሎ በማነፍ በውድድሩ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቱም ይታወሳል።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲምቦ አለማየሁ የአለም አትሌቲክስ የአመቱ የወደፊት ተስፋ የተጣለባት አትሌት በመባል መሸለማንም የዓለም አትሌቲክስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አትሌቷ በቡዳፔስት በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና እና በፓሪሱ ኦሎምፒክ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሀገሯን ወክላ ውጤት ማስመዝገቧ ይታወሳል።
በተጨማሪ በኦሎምፒክ የ 3000ሜ መሰናክል ውድድር አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች።
በዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሽልማት ለኔዘርላድስ የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲፈን ሀሰን የአመቱ ምርጥ ሴት አትሌትና ከስታድየም ውጪ በተደረጉ ውድድሮች የ2024 ምርጥ ሴት አትሌት ሽልማቶች በማሸነፍ ችላለች።
ቦትስዋናዊው አትሌት ሌትሲሌ ቶቦጎ በዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሽልማት የአመቱ ምርጥ ወንድ አትሌትና የትራክ ላይ ውድድር ምርጥ አትሌት ተብሎ ተመርጧል።