አትሌት ትግስት አሰፋ በዓለም ምርጥ የዓመቱ አትሌቶች ዝርዝር ለመጨረሻው ዙር አለፈች
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትግስት አሰፋ የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤት ነች
አትሌት ለተሰንበት ግደይ "የስፖርታዊ ጨዋነት" ሽልማት ከመጨረሻ ሶስት ዕጩዎች አንዷ ሆናለች
የማራቶን ባለሪከርዷ አትሌት ትግስት አሰፋ ለአለም አትሌቲክስ በዓለም ምርጥ የዓመቱ አትሌቶች ዝርዝር ለመጨረሻው ዙር ውድድር አለፈች።
የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተያዘው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶችን ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በመጀመሪያው ዙር 11 ምርጥ የዓለማችን አትሌቶች ዝረዝር ውስጥም ኢትዮጵያዊያን ሁለት አትሌቶች የተካተቱ ሲሆን የ 5 ሺህ ሜትር ባለ ሪከርዷ ጉዳፍ ጸጋዬ እና የማራቶን ባለሪከርዷ አትሌት ትግስት አሰፋ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ አትሌቶች ነበሩ።
ዎርልድ አትሌቲክስ በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው መረጃ በውድድሩ ለመጨረሻ ዙር ያለፉ አትሌቶችን ዝርዝር አውጥቷል።
በዚህም የማራቶን ባለሪከርዷ ኢትዮጵያውቷ አትሌት ትግስት አሰፋ ለመጭረሻ ዙር ውድድር ከቀረቡ አትሌቶች መካከል እንዷ ሆናለች።
ከአትሌት ትግስት አሰፋ በተጨማሪ ኬንያዊቷ አትሌት ፍይዝ ኪፕዬጎን፣ ጃማይካዊቷ ሸሪካ ጃክሰን፣ የኔዘርላንዷ የ400 ሜትር ተወዳዳሪ ፌምኬ ቦል እንዲሁም ቬንዙዌላዊቷ የርቀት ዘላይ ዩሊማር ሮጃስ ለመጨረሻ ዙር በእጩነተ ቀርበዋል።
አትሌት ለተሰንበት ግደይም ለአለም አትሌቲክስ "የስፖርታዊ ጨዋነት" ሽልማት ከመጨረሻ ሶስት ዕጩዎች አንዷ መሆኗ ይታወሳል
ከወራት በፊት በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮ በ10ሺ ሜትር የሴቶች ሩጫ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ያሳየችው በውድድሩ ላይ የወደቀችውን አትሌት ሲፋን ሀሰንን ወደኋላ በመመለስ በማቀፍ ባሳየችው ስፖርታዊ ጨዋነት ለሽልማት መታጨቷን ይታወቃል።
የመጨረሻ አሸናፊ ምርጥ የዓመቱ ሴት እና ወንድ አትሌቶች ምርጫ ደግሞ ከህዳር 2-3 ቀን 2016 ዓም ይፋ ይደረጋል ተብሏል።