የዓለም ባንክ ከዓመታዊ የፋይናነስ ዳጋፉ 45 በመቶውን ለአየር ንብረት እንደሚያውል አስታወቀ
የዓለም ባንክ ከኮፕ28 ጎን ለጎን ትልቅ የፋይናንስ ፓኬጅ ይፋ አድርጓል
ኮፕ28 አለምን የሚታደጉ በርካታ ስምምነቶች ተደርሰውበታል - የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት
የዓለም ባንክ ከተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP28) ጎን ለጎን ትልቅ የፋይናንስ ጥቅል አስታወቀ።
የፋይናንስ ጥቅሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጫና በተሻለ ሁኔታ እንዲቋቋሙ ለመርዳት እና ለሁሉም የተሻለ ዓለም ለመፍጠር ያለመ ነው።
በዚህም በፈረንጆቹ ከሐምሌ 1 ቀን 2024 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2025 ድረስ ባለው የበጀት ዓመት ከዓመታዊ ፋይናንስ ድጋ 45 በመቶው ከአየር ንብረት ጋር ለተያያዙ ፕሮጀክቶች መድቧል።
የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ከኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ጉባኤው የተለያዩ አካላትን በአንድ ጠረጴዛ ለውይይት ማስቀመጡን ነው ያነሱት።
ከአካታችነቱ ባሻገርም አለምን እየፈተኑ ለሚገኙ ጉዳዮች ግልጽ እና ቀነ ገደብ የተቀመጠላቸው የመፍትሄ ሃሳቦች የተነሱበት መሆኑንም አብራርተዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚታይ ለውጥ የሚፈልጉ አካላት ለደረሱት ስምምነት መፈጸም ቁርጠኛ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።
በኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ይፋ የተደረገው የ30 ቢሊየን ዶላር ፈንድም የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቀነስ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ነው የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ያነሱት።
ፈንዱ በተለይ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በስፋት ለሚስተዋልባቸው ታዳጊ ሀገራት ትልቅ የምስራች መሆኑንም በማከል።
በዱባይ መካሄዱን በቀጠለው የኮፕ28 ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተኑ ለሚገኙ ሀገራት ዋነኞቹ በካይ ሀገራት ሊያደርጉት ስለሚገባው የፋይናንስ ድጋፍ ምክክር እየተደረገ ነው።
አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም በታዳሽ ሃይል ልማት ሽግግር ሊያደርጉት ስለሚችሉት ድጋፍ የሚደረገው ንግግር ቀጥሏል።
ኦክስፋም በአየር ንብረት ፋይናንስ ላይ ባደረገው አዲስ ጥናት የበለጸጉ ሀገራት ከእርዳታ ይልቅ ብድር በመስጠት ድሀና አቅመ ደካማ ሀገራት ከአየር ንብረት ቀውስ ለመከላከል የሚሰሩትን ስራ እየጎተቱ መሆናቸውን አመልክቷል።
ጥናቱ በተዘዋዋሪ መንገድ የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ለታዳጊ ሀገራት ለመክፈል ቃል የገቡት 100 ቢሊዮን ዶላር የተገደበ መሆኑንም ጠቁሟል።
በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የኮፕ28 ጉባኤም የበለጸጉት ሀገራት ቃል የገቡትን 100 ቢሊየን ዶላር እንዲሰጡ እና የፋይናንስ ተቋማትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ለሚያግዙ ስራዎች በቂ ድጋፍና ብድር እንዲያቀርቡ ተጠይቆበታል።