ከ10 ዓመታት ውይይት በኋላ የዓለምን ውቅያኖሶች ለመጠበቅ ታሪካዊ ስምምነት ተደረሰ
ስምምነቱ 30 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ባህር ለመጠበቅና ለማዳን ያለመ ነው ተብሏል
የባህር ውስጥ ህይወት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአሳ ማስገር እና በማጓጓዣዎች ፍሰት አደጋ እንደተጋረጠበት ተነግሯል
ከ10 ዓመታት ውይይት በኋላ የዓለምን ውቅያኖሶች ለመጠበቅ ታሪካዊ ስምምነት ተደረሰ።
ሀገራት የዓለምን ውቅያኖሶች ለመጠበቅ ታሪካዊ የተባለ ስምምነት ከ10 ዓመት ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስምምነቱ በፈረንጆች 2030፤ 30 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ባህር "ጥብቅ ስፍራ" በማድረግ የባህር ተፈጥሮን ለመጠበቅ እና ለማዳን ያለመ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ የተደረሰው ከ38 ሰዓታት ውይይት በኋላ በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ነው።
ድርድሩ በገንዘብ እና በአሳ ማስገር መብቶች ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ለዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል።
በውቅያኖስ ጥበቃ ላይ የመጨረሻው ዓለም አቀፍ ስምምነት የተፈረመው ከ40 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1982 ነው። ህጉም "የተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ስምምነት" በመባል ይታወቃል።
ቢቢሲ እንደዘገበው 'ከፍተኛ ባህር' ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ዓለም አቀፍ ውሃ ሁሉም ሀገራት የአሳ ማጥመድ፣ የመርከብ አገልግሎት እና ምርምር የማድረግ መብት አላቸው።
ነገር ግን ከእነዚህ ውሃዎች ውስጥ 1 ነጥብ 2 በመቶዎቹ ብቻ የተጠበቁ ናቸው ተብሏል።
ከእነዚህ ከተጠበቁ አካባቢዎች ውጭ የሚኖረው የባህር ውስጥ ህይወት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአሳ ማስገር እና በማጓጓዣዎች ፍሰት አደጋ ተጋርጦበታል ነው የተባለው።
በዓለም አቀፍ የባህር ውስጥ ዝርያዎች ላይ በተደረገ የቅርብ ጊዜ ግምገማ ወደ 10 በመቶ የሚጠጉ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲል የዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ህብረት ገልጿል።
በስምምነቱ በሚከለሉ ስፍራዎች ምን ያህል አሳ ማጥመድ እንደሚቻል፣ የመርከብ መስመሮች እና ጥልቅ የባህር ማዕድን ፍለጋ ስራዎች ላይ ገደብ ያስቀምጣል ተብሏል።
የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች የባህር ማዕድን የማውጣት ሂደቶች የእንስሳት እርባታ ቦታን በድምፅ ብክለት እንደሚረብሹ እና ለባህር ህይወት መርዝ ሊሆኑ እንደሚችሉ አሳስበዋል።