በሃውሲ አማጽያን የተመለመሉ 2 ሺ ህጻናት በየመን ጦርነት ሞተዋል- ተመድ
አማጽያኑ በቅርቡ በዩኤኢ የድሮን ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጦርነቱ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ
ተመድ አማጽያኑ ከእድሜ በታች ህጻናትን ከመመለመል እንዲቆጠቡ አሳስቧል
በሃውሲ አማጽያን የተመለመሉ 2 ሺ ህጻናት በየመን ጦርነት መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት የባለሙያዎች መርማሪ ቡዱን ገለጸ፡፡
መርማሪ ቡዱኑ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት እንዳስታወቀው፤ በኢራን እንደሚታገዝ የሚነገርለት የሃውሲ አማጺ ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ ከእድሜ በታች የሆኑ ህጻናትን በመመልመል በአስከፊ ጦርንት እየማገዳቸው ይገኛል፡፡
አማጺ ቡድኑ አሁንም በርካታ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማእከላትን በማቋቋምና ህጻናትን ለውትድርና በመመልመል ለጦርነት እየተዘጋጀ እንደሆነም ነው የመርማሪ ቡዱኑ ሪፖርት የሚያመለክተው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እንደፈረንጆቹ 2015 በየመን የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ እስካሁን ከ10 ሺ በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከነዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ያለፍላጎታቸው ለውትድርና የተመለመሉ ህጻናት ናቸው፡፡
በአማጽያኑ ተገደው ለጦርነት ከተመለመሉ ህጻናት “በ2020 1 ሺ 406 በ2021 ደግሞ ሌሎች 562 ህጻናት ሞተዋል” ሲልም ነው መርማሪ ቡድኑ በ300 ገጽ ባዘጋጀው ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው፡፡
ህጻናቱ በማስልጠኛ ማዕከላት ቆይታቸው 'ሞት ለአሜሪካ '፣ 'ሞት ለእስራኤል' የመሳሰሉትንና ሌሎችንም መፈክሮች እንደሚያንጸባርቁም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
"በአንድ ማሰልጠኛ ማእክል የ7 ዓመት ልጅ የጦር መሳርያዎችን እና ሮኬቶችን ሲፈታና ሲገጥም ማየት የተለመደ ነው"ም ነው ያለው ኤ.ፒ በዘገባው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተመድ መርማሪ ቡድን አማጽያኑ ከመሰል ተግባር እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
በተለያዩ ማዕቀቦች ውስጥ የሚገኙት አማጽያኑ ምንም እንኳን በዩኤኢ መከላከያ ቢከሽፍም ዛሬ ጭምር ወደ አቡ ዳቢ ሚሳዔል አስወንጭፈዋል፡፡
ይህ ለሶስተኛ ጊዜ የሆነ ነው፡፡ በቅርቡ በፈጸሙት የመጀመሪያ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን ማውገዙና ለዩኤኢ ያለውን አጋርነት መግለጹ ይታወሳል፡፡