35 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ
በሳዑዲ አረቢያ ባሉ እስር ቤቶችና መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አሉ
ኢትዮጵያ ወደ 15 ሀገራት አዲስ አምባሳደሮችን ማሰማራቷን ሚንስቴሩ ገልጿል
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በሳዑዲ አረቢያ ባሉ እስር ቤቶች እና መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አሉ።
እነዚህን ዜጎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከሳዑዲ መንግስት ጋር ውይይቱ እንደቀጠለ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ዲና እስካሁን ባለው ሂደት 35 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ተመዝግበዋል ብለዋል።
በቀጣይ ጥቂት ቀናት ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያንን የመመለስ ስራው እንደሚጀመር እና ፍላጎት ያላቸውን ሌሎች ተጨማሪ ዜጎችን ለመለየት ምዝገባው እንደሚቀጥልም አክለዋል።
የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማሳለጥም ወደ ተለያዩ አገራት አዳዲስ ዲፕሎማቶች መላካቸውንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አክለው ተናግረዋል ።
አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ፓኪስታን፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ኤርትራ ፣ አውስትራልያ ፣ ዚምባብዌ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሩዋንዳ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ስዊድን፣ ኩባ፣ ኮቲዲቯር፣ እና ሱዳን የአምባሳደሮች ምደባ የተደረገባቸው አገራት ናቸው።
የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሱዳን ባለመረጋጋት ውስጥ በመሆኗ እስካሁን ድርድሩ ሊጀመር እንዳልተቻለም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ድርድር ሱዳን ወደ መረጋጋት ስትመጣ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ይቀጥላልም ተብሏል።