ሞሮኮ ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ለመሆን ፖርቹጋልን ትገጥማለች
በኳታሩ የአለም ዋንጫ እስካሁን አንድ ጎል ብቻ ያስተናገዱት የአትላስ አንበሶቹ፥ 12 ጎሎችን ካስቆጠሩት ሴሌሳዎቹ ጋር ይፋለማሉ
ምሽት 4 ስአት ላይ የሚደረገው የእንግሊዝና ፈረንሳይ ፍልሚያም ተጠባቂ ነው
ብራዚል እና ኔዘርላንድስን ከግማሽ ፍጻሜው ውጭ ያደረገው የኳታሩ የአለም ዋንጫ ዛሬ ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ሞሮኮ ከፖርቹጋል ፤ እንግሊዝን ከፈረንሳይ የሚያገናኙት ጨዋታዎች በጣም ተጠባቂ ናቸው።
1. የአትላስ አንበሶቹ የአዲስ ታሪክ ፍልሚያ
12 ስአት ላይ በአልቱማማ ስታዲየም ፖርቹጋልን የምትገጥመው ሞሮኮ የኳታሩ የአለም ዋንጫ ጉዞዋ መቋጫ ነው ወይስ አዲስ ታሪክ ማጻፊያ? ብዙዎች የሚነጋገሩበት ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
ቤልጂየም እና ስፔን የመሰሉ ሀገራትን ጥለው ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉት የአትላስ አንበሶቹ፥ በአለም ዋንጫ ታሪክ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰ የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡድን ለመሆን ነው ሴሌሳዎቹን የሚገጥሙት።
ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ የገባበት ብሄራዊ ቡድን በአልቱማማ ስታዲየም ታሪክ ያጽፍ ዘንድ የሀገሪቱ አየርመንገድ በቀን ሰባት በረራዎችን ወደ ዶሃ እያደረገ ነው።
በኳታር የሚገኙ ከ15 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ዜጎችም ስታዲየሙን በቀዩ ሰንደቅና በህብረ ዝማሬ ያደምቁታል።
አሰልጣኛቸው ዋሊድ ሬግራጊም ከሁሉም የአፍሪካ እና አረብ ሃገራት ያላቸው ድጋፍ ለውጤት እንደሚያበቃቸው ተናግረዋል።
ሩብ ፍጻሜውን በመቀላቀል ከአፍሪካ ሀገራት 4ኛ የሆነችው የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር ጠንካራ የመከላከል ብቃቷን በአለም ዋንጫው አሳይታለች።
በነአሽራፊ ሃኪሚ እና ሃኪም ዚያች የሚመራው የፊት መስመርም የአውሮፓ ሃያላኑን ሲፈታተን ታይቷል።
ስፔንን በመለያ ምት ከሩብ ፍጻሜው ውጭ ያደረጉት የአትላስ አንበሶቹ ስዊዘርላንድን 6 ለ 1 በመርታት ሩብ ፍጻሜውን ከተቀላቀሉት ሴሌሳዎቹ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ግን ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ፖርቹጋል በኳታር በስምንት ተጫዋቾቿ 12 ጎሎችን ማስቆጠሯም የፊት መስመሯ ለአፍሪካዋ ሃገር ፈታኝ መሆኑ እንደማይቀር ያሳያል።
የክርስቲያኖ ሮናልዶ መሰለፍ ጉዳይ ግን እስካሁን ግልጽ አልተደረገም።
2. የእንግሊዝና ፈረንሳይ ትንቅንቅ
አል ባይት ስታዲየም ምሽት 4 ስአት ላይ የዋንጫ ጨዋታ የሚመስል ፍልሚያን ያስተናግዳል።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ 12 ጎሎችን ያስቆጠረችው እንግሊዝ ፥ 9 ጎሎችን አስቆጥራ ለዋንጫው ሰፊ ግምት የተሰጣትን ፈረንሳይ ትገጥማለች።
በጋሬዝ ሳውዝጌትና ዲዲየር ዴሻምፕ የሚመሩት የአውሮፓና የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኖቹ፥ በአለም ዋንጫው ከአራት አስርት በኋላ ይገናኛሉ።
በ1982ቱ የስፔን የአለም ዋንጫ በሚሼል ፕላቲኒ የሚመሩት ሰማያዊዮቹ የ3 ለ 1 ሽንፈት ማስተናገዳቸው የሚታወስ ነው።
ሶስቱ አናብስት በ1966 ብቸኛውን የአለም ዋንጫቸውን ሲያነሱም ካሸነፏቸው ሀገራት መካከል አንዷ ፈረንሳይ መሆኗን ታሪክ ያወሳል።
በሩብም ሆነ በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ተገናኝተው የማያውቁት ሁለቱ ሀገራት ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በኳታር አምስት ጎሎችን በማስቆጠር የ2022ቱን የፊፋ የወርቅ ጫማ ሽልማት ለመውሰድ እየመራ ያለው ኪሊያን ምባፔ እና የምንጊዜም የፈረንሳይ ጎል አስቆጣሪነትን ክብር የተቀዳጀው ኦሊቨር ጂሩድ የሶስቱን አናብስት የግብ ክልል ይቆጣጠሩታል።
የዋይኒ ሩኒን የምንጊዜም የእንግሊዝ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን (53) ለመስበር ሁለት ጎሎች ብቻ የቀሩት ሃሪ ኬን ደግሞ የሰማያዊዮቹ ስጋት ነው።
የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ ከሞሮኮ አልያም ከፖርቹጋል ጋር በግማሽ ፍጻሜው ይፋለማል።