በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ምክንያት 40 ሚሊየን አፍሪካዊያን ለምግብ እጥረት እንደሚጋለጡ አሜሪካ ገለጸች
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 165ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
አፍሪካ በአውሮፓ የእርስ በርስ ጦርነት ገለልተኛ ነኝ ብትልም ከምዕራባውያን ጎን እንድትቆም ዘመቻው ቀጥሏል
በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ምክንያት 40 ሚሊየን አፍሪካዊያን ለምግብ እጥረት እንደሚጋለጡ አሜሪካ ገለጸች።
ዩክሬን የሰሜን ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ጦርነት የጀመሩት።
165 ቀናትን ባስቆጠረው የእስካሁኑ ጦርነት ከሁለቱ ሀገራት ባለፈ የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
በዚህ የአውሮፓዊያን የእርስ በርስ ጦርነት በአሜሪካ የሚመራው የምዕራባውያን ህብረት ሩስያን ከተቀረው ዓለም ለመነጠል የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን በመከወን ላይ ይገኛል።
የዚሁ ዘመቻ አንድ አካል የሆነው በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ አፍሪካን ጎብኝተዋል።
አምባሳደሯ በዩጋንዳ ከፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት 40 ሚሊዮን አፍሪካዊያን የምግብ ደህንነት አደጋ ላይ መውደቁን ተናግረዋል።
በአውሮፓ የእርስ በርስ ጦርነት ገለልተኛ ነኝ የምትለው አፍሪካ አቋም እንድትይዝ በተለይም ምዕራባዊያንን እንዲደግፉ አሜሪካ በመወትወት ላይ ትገኛለች።
አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በአፍሪካ በነበራቸው ጉብኝት ላይ እንዳሉት "አፍሪካ በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ውግንና እንዲኖራት እንደማትፈልግ እናውቃለን፤ ነገር ግን እውነታውን እንዲረዱ እንፈልጋለን" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኮሮና ቫይረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭቶች ለዓለም ምግብ ቀውስ ምክንያቶች ናቸው ያሉት አምባሳደሯ ረሀብን እንደ ጦርነት መጠቀም ግን ለምግብ እጥረቱ ትልቁ ምክንያት መሆኑን አፍሪካዊያን እንዲረዱ እንደሚፈልጉም አክለዋል።
ሩሲያ ሆን ብላ የዩክሬን ከፍተኛ ምርት ሰጪ አካባቢዎችን መቆጣጠሯን ፣ የሰብል ማሳዎችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ላይ መሆኗን አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ተናግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ምዕራብ አፍሪካን የጎበኙት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በተመሳሳይ አፍሪካ በሩሲያ ላይ ተለሳልሳለች ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ሩሲያ በበኩሏ ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል በምዕራባዊያን የሚቀርብባትን ክስ ውድቅ ያደረገች ሲሆን ለምግብ ዕጥረቱ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብን ምክንያት መሆኑን ጠቅሳለች።