10ኛው የአለም የመንግስታት ጉባኤ በዱባይ እየተካሄደ ነው
ጉባኤው በቱርክና በሶሪያ ርዕደ መሬት ህይወታቸው ላለፈ ወገኖች የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጀምሯል
በጉባኤው ከ20 በላይ ሀገራት መሪዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የተቋማት መሪዎች እና ምሁራን እየተሳተፉ ነው
የ2023 የአለም የመንግስታት ጉባኤ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ከመጀመሩ አስቀድሞም በቱርክና በሶሪያ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ከ 33 ሺህ በላይ ሰዎች የህሊና ጸሎት ተደርጓል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሞሃመድ አብዱላህ አል ገርጋዊ፥ ከህሊና ጸሎቱ በኋላ “የ10 አመት ህዳሴ” የሚል ርዕስ ያለውን የውይይት መድረክ አስጀምረዋል።
በጉባኤው የግብጽ እና ሴኔጋል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የ20 ሀገራት መሪዎች እና ከ250 በላይ ሚኒስትሮችም ታድመዋል።
ከ150 ሀገራት በላይ የመጡ ምሁራን፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና የቢዝነስ ተቋማት መሪዎችም በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ከ80 በላይ አለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መሪዎችም በዚህ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የአለም የመንግስታት ጉባኤ የአለም መጻኢ መንግስታት ምን መልክ እንደሚኖራቸው የሃሳብ ልውውጥ የሚደረግበትና የመንግስት እና የግል ዘርፎች ትስስር መፍጠሪያ መድረክ ነው።
በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት የታዩ ስኬታማ ተግባራትም እንዲስፋፉ ጉባኤው ትልቅ እድል ይፈጥራል ነው የተባለው።
ኤምሬትስ በየአመቱ የምታዘጋጀው የአለም የመንግስታት ጉባኤ መንግስታት በአሁኑ ወቅት ፈተና የሆኑባቸው ጉዳዮችና መውጫ መንገዱን የሚያመላክቱ ሃሳቦች ይንሸራሸሩበታል።
በተለይ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የአለምን ውስብስብ ችግሮች ማቃለል የሚያስችሉ ምክክሮች ይደረጋሉ ።
ለሶስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ በርካታ የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።
የአለማችን የግዙፍ ተቋማት መሪዎችና ሃሳብ አፍላቂዎች የአሁኑን እና መጪውን ጊዜ ፈተናዎች በማንሳት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው።