የአዕምሮ ህመም በወረርሽኝ ደረጃ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ጥናት አመላከተ
ጭንቀት ፣ ድብርት እና ሌሎችም የአዕምሮ ህመሞች በአለም አቀፍ ደረጃ በአስጊ ደረጃ እየተስፋፉ ነው ተብሏል
በእነዚህ በሽታዎች የተነሳ የሰዎች የስራ ምርታማነት ሲቀንስ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ይበልጥ ተጋላጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ጥናቱ ገልጿል
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ እንደሚገኝ ጥናት አመላክቷል፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ የጥናት ውጤት ጠቅሶ ባስነበበው ዘገባ ድብርት ፣ ጭንቀት ፣ መገለል እና ሌሎችም ከአዕምሮ ህመም ጋር የሚያያዙ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ እየተስፋፉ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
የህመሞቹ መስፋፋት በሁሉም የስራ ዘርፎች የሰዎችን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰው ሲሆን በፋይናነስ እና በኢንሹራንስ አመራርነት የሚሰሩ ሰዎች በ17 መቶ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል፡፡
የፋይናስ ዘረፍ ተቀጣሪዎች ከበሽታዎቹ ጋር በሚያደርጉት ግብግብ ለህክምና ለመድሀኒት እና ለሌሎች ወጪዎች እስከ 6 ሺህ ዶላር ድረስ ወጪ እንደሚያደርጉ ጥናቱ ገልጿል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት እና አለም አቀፉ የሰራተኞች ማህበር በጋራ ባወጡት ሪፖርት በአዕምሮ ጤና መታወክ ምክንያት በየአመቱ 12 ቢሊየን የስራ ሰአቶቸ እንደሚባከኑ በተጨማሪም አለም አቀፍ ኢኮኖሚ አንድ ትሪሊየን ዶላር እንደሚያሳጣ አስታውቀዋል፡፡
በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የኤፒዲሚዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬት ፒኬት የችግሩ ስፋት በተለይም በወጣቶች ላይ በጣም አሳሳቢ ነው ሲሉ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናግረዋል።
ብሪታንያን ለአብነት ያነሱት ፕሮፌሰሯ በ2017 በሀገሪቱ ከ9 ወጣቶች ወይም ታዳጊዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ ጤና መታወክ ተጠቂ ሲሆን ፤ይህ ቁጥር በ2023 በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ከአምስት ወጣቶች አንዱ ህመምተኛ ወደ መሆን ተሸጋግሯል ነው ያሉት፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለድብርት ጭንቀት እና ሌሎችም የአዕምሮ በሽታዎች መጨመር ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ጦርነት እና ግጭት እንዲሁም የማህበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቃም ቀዳሚ ምክንያት ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡
እንደ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ በአሁኑ ወቅት 280 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በድብርት የሚሰቃዩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 28 በመቶውን የሚሸፍኑት ከ18-29 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡
ጭንቀትን በተመለከተ አራት በመቶ የአለም ህዝብ በአዕምሮ ጭንቀት ውስጥ የሚኖር ሲሆን አጠቃላይ ቁጥሩ ደግሞ ከ301 ሚሊየን እንደሚሻገር መረጃው አመላክቷል፡፡