ፊንላንድ ለ7 ተከታታይ አመት የአለማችን ቀዳሚዋ ደስተኛ ሀገር ሆነች
የኖርዲክ ሀገራት በ2024ቱ የአለም ሀገራት የደስተኝነት ደረጃ ቀዳሚነታቸውን አስጠብቀው ቀጥለዋል።
ፊንላንድ ለሰባተኛ ተከታታይ አመት የአለማችን ቁጥር አንድ ደስተኛ ሀገር የተባለች ሲሆን፥ ዴንማርክ፣ አይስላንድ እና ስዊድን ይከተላሉ።
በጋዛ በሃማስ ላይ ጦርነት ካወጀች ስድስት ወር ሊሞላት የተቃረበችው እስራኤል በበኩሏ አምስተኛ ደረጃን ይዛለች።
አለማቀፉ የደስታ ቀን በመንግስታቱ ድርጅት ከ2012 ጀምሮ እውቅና ተሰጥቶት በፈረንጆቹ መጋቢት 20 በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
በዚህ እለት ገለልተኛ ቡድን የሚያጠናውና ከ143 በላይ ሀገራትን ዜጎች በመጠየቅ የሚከናወነው የአለም የደስተኝነት ደረጃ ይፋ ይደረጋል።
ሪፖርቱ የሀገራቱ ዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ የማህበራዊ ድጋፍ፣ የጤና መድህን ዋስትና፣ ነጻነት፣ ለጋስነት እና ሙስና ዙሪያ የሚሰማቸውን ከ1 እስከ 10 ነጥብ እንዲሰጡ ተደርጎ ነው ደረጃው የሚወጣው።
በ2024ቱ የአለም የደስተኝነት ሪፖርት ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ሉግዘንበርግ፣ ስዊዘርላንድ እና አውስትራሊያ ከ5ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በምዕራባውያን ሀገራት ደስታ የሚርቃቸው ወጣቶች መጠን እየጨመረ መሆኑን የሚያሳየው ሪፖርቱ፥ አሜሪካ እና ጀርመን ከ10 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ 20ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል ብሏል።
አሜሪካ እና ጀርመን አረብ ኤምሬትስን ተከትለው 24ኛ እና 25ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በ2024ቱ የደስተኝነት ሪፖርት ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩት ሀገራት የምዕራብ አውሮፓዎቹ ሰርቢያ፣ ቡልጋሪያ እና ላቲቪያ ናቸው።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከ10 ነጥብ 3 ነጥብ 86 በማስመዝገብ ከ143 ሀገራት 130ኛ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፥ ደስታ ከራቃቸው 20 ሀገራት ደግሞ 14ኛ ሆናለች።
አፍጋኒስታን በአለማችን ደስታ ከራቃቸው ሀገራት በዚህ አመትም በቀዳሚነት የተቀመጠች ሲሆን፥ ሊባኖስ፣ ሌሴቶ፣ ሴራሊዮን፣ ኮንጎ (ኪንሻሳ) እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
aXA6IDE4LjIyMy4xMTQuMTQyIA==
ejasoft island