በ2022 የተካሄዱ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምዶች የትኞቹ ናቸው?
የሩስያ ዩክሬን ጦርነት በተጀመረ ማግስት አሜሪካ መራሽ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምዶች በተለያዩ ሀገራት ተደርገዋል
ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራንን “አደብ ያስገዛሉ” የተባሉ የጦር ልምምዶችም በተደጋጋሚ ቢካሄዱም የተፈለገውን ውጤት ግን አላስገኙም
የፈረንጆቹ 2022 አለምን ከጫፍ ጫፍ ተጎጂ ያደረገው የሩስያና ዩክሬን ጦርነት የተጀመረበት ነው።
ሞስኮ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ በሚል ወደ ዩክሬን ዘልቃ ከገባች በኋላ አለም በሁለት ጎራ ተከፍሏል።
ከኬቭ ጋር አጋርነታቸውን ያሳዩ ሀገራትም የጦር መሳሪያዎችን እየላኩ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችንም ማድረጋቸው ጦርነት አድማሱን እንዳያሰፋው ስጋት እየጫረ 10 ወራት ተቆጥረዋል።
ይህ የፈረንጆቹ አመት በቻይና እና ታይዋን ፍጥጫ በሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ መጨመር ምክንያትም ሀገራት ለቤጂንግ እና ፒዮንግያንግ መልዕክት ለመስደድ ያለሙ ወታደራዊ ልምምዶችን ሲያካሂዱ ታይቷል።
አል አይን አማርኛም በዚህ አመት የተካሄዱ ወታደራዊ ልምምዶችን በወፍ በርረ ያስቃኛችኋል።
የሩስያ ወታደራዊ ልምምድ በኩሪልስ
ሩስያ በመጋቢት ወር 2022 በኩሪልስ ያደረገችው ወታደራዊ ልምምድ ብዙ ውዝግቦችን ያስነሳ ነበር። ሞስኮ ጃፓን ሉአላዊ ግዛቶቼ ናቸው በምትላቸው የኩሪልስ ደሴቶች ያደረገችው ልምምድ ከቶኪዮ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ከቷት እንደነበርም የሚታወስ ነው። ልምምዱ ሩስያ ከጃፓን ጋር የሰላም ንግግር ባቋረጠች ማግስት ተካሂዷል።
የፔሎሲ ጉብኝትና የቻይና ወታደራዊ ልምምድ
የአሜሪካ ኮንግረንስ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በ2022 ነሃሴ ወር በታይውን ጉብኝት ማድረጋቸው የቻይና ሹማምንትን ክፉኛ አስቆጥቷል። ዋሽንግተን ለራስ ገዟ ታይፒ ያሳየችው ድጋፍና የመሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ያበሳጫት ቤጂንግ ታይዋንን በስድስት አቅጣጫዎች ዘግታ በታይዋን ሰርጥ የአየርና የባህር ሃይሏን ያሳተፈ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች። ግልጽ መልዕክቱም ታይፒ የቻይና አካል መሆኗንና የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደማትታገስ ለአሜሪካ ማሳየት ነበር።
የታይዋን አጻፋ
ከቻይና ወታደራዊ ሃይል ልምምድ በኋላ ታይዋንም የአንድ ቀን ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች። በዚህም “ከቻይና ሊቃጣ የሚችል ወረራን” እንዴት መከላከል ይቻላል የሚለውን በኮምፒተር የታገዘ ልምምድ ማድረጓ ነው የሚታወሰው። ታይፒ በዚህ ልምምድ ሚሳኤል የሚታጠቁ እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶቿን በማሳየትም ለቤጂንግ መልዕክት ለመስደድ ሞክራለች።
የምስራቁ ጥምረት
ቻይና እና ሩስያ “ምስራቅ 2022” የሚል ስያሜ የሰጡትን ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ያደረጉትም በዚሁ የፈረንጆች አመት ነሃሴ ወር መጨረሻ ነው። ለስድስት ቀናት በተካሄደው ልምምድ ህንድ፣ ቤላሩስ እና ታጂኪስታንም ተሳታፊዎች ነበሩ። ሩስያ እና ቻይና በድንበራቸው ዙሪያ በ13 የተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉትን ወታደራዊ ልምምድ ለምዕራባውያን ማስጠንቀቂያን ለመላክ ተጠቅመውበታል።
የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ልምምድ
ከ60 በላይ ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈችው ሰሜን ኮሪያ በ2022 የአሜሪካና የቀጠናው ስጋት ሆና ከርማለች። አሜሪካም በሃዋይ የቀጠናው አጋሮቿን ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጠርታ የፒዮንግያንግን ተጽዕኖ የሚመክት ልምምድ አድርጋለች። ሚሳኤል ሲተኮስ ማስጠንቀቂያ በፍጥነት የሚሰራጭበትና የባለስቲክ ሚሳኤል የወደቀበትን ቦታ የመለያ መንገደች በሶስቱ ሀገራት ወታደራዊ ልምምድ ተዳሰዋል።
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በዚህ አመት አራት ጊዜ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውም ግልጽ የጦርነት ዝግጅት ነው ያለችው ፒዮንግያንግ ሚሳኤል በመተኮስ ኩርፊያዋን ስትገልጽ እንደነበር ይታወሳል።
“የቀዩ ሞገድ 5”
በግንቦት 30 2022 በምዕራባዊ ሳኡዲ አረቢያ ጂዳ ከተማ የቀይ ባህር ደህነንትን ለማረጋገጥ የሚረዳ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተደርጓል። የቀይ ባህር የንግድ መስመርን ከባህር ላይ ጠላፊዎች ለመጠበቅ ባለመው ልምምድ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና የመን ተሳታፊ ነበሩ። የሳኡዲ ባህር ሃይል፣ የድንበር ጠባቂ ዘብና ሌሎች የጸጥታ ባለሙያዎችም በወታደራዊ ልምምዱ መሳተፋቸው የሚታወስ ነው።
“የአፍሪካ አናብስት 2022”
ሞሮኮን ጨምሮ 10 የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት ወታደራዊ ልምምድ በሰኔ 20 2022 በሞሮኮ ተከሂዷል። “የአፍሪካ አናብስት 2022” የሚል ስያሜ በተሰጠው ወታደራዊ ልምምድ ላይ ከ7 ሺህ በላይ የሞሮኮ ወታደሮች ተሳትፈዋል።የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጣሊያን እና የሰሜን ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶም የልምምዱ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ይታወሳል።
ሄርኩለስ 2 ልምምድ
ግብጽ በነሀሴ 21 2022 በሞሃመድ ናጉይብ ወታደራዊ ጣቢያ ከአጋር ሀገራት ጋር ያደረገችው ልምምድም በዚህ አመት ከተደረጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚጠቀስ ነው። በዚህ ልምምድ ላይ የሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ ግሪክ እና ቆጵሮስ የተሳተፉ ሲሆን፥ አሜርካ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ባህሬን በታዛቢነት መገኘታቸው መገለጹ አይዘነጋም።
የፓስፊክ ውቅያኖስን የጦር ሜዳ ያስመሰለው ልምምድ
የጃፓን እና አሜሪካ ባህር ሃይሎች በፓስፊክ በተከታታይ የሚያደርጉትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በዚህ አመትም አጠናክረው ቀጥለዋል። በህዳር 20 2022ትም ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል መኩራዋን ስትደጋግም ብሪታንያ መርከቧን ወደዚሁ አካባቢ ልካለች። አውስትራሊያ እና ካናዳም የጋራ ልምምዱን ተቀላቅለው ነበር። በአምስቱ ሀገራት የ10 ቀናት ወታደራዊ ልምምድ ከ36 ሺህ በላይ ወታደሮች፣ 30 የጦር መርከቦችና 340 አውሮፕላኖች ተሳትፈዋል።
ኢራን ላይ ያነጣጠሩት የእስራኤል የጦር ልምምዶች
እስራኤል ከአሜሪካ ጋር ግዙፍ ነው ያለችውን ወታደራዊ ልምምድ በህዳር ወር መጨረሻ አድርጋለች። ዋነኛው የልምምዱ አላማም የኢራንን ስጋትነት ወደ ዜሮ ማውረድ ነው። በታህሳስ 5 2022ትም ከእስራኤል አየር ሃይል ከፈረንሳይ አቻው ጋር በቴል አቪቭ ሰማይ “የምስራቁ ንፋስ” የሚል ስያሜ የሰጠውን ልምምድ አድርጓል። እስራኤል፥ ኢራን ታስታጥቀዋለች የምትለውን የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ለመመከትም ከ13 ሺህ በላይ ወታደሮች የተሳተፉበትን ወታደራዊ ልምምድ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ማድረጓ ይታወሳል።
በአጠቃላይ በ2022 የተደረጉ ወታደራዊ ልምምዶች አብዛኞቹ በሩስያ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን ላይ ያነጣጠሩ ስለመሆናቸ ተደጋግሞ ተነስቷል።
ሀገራት አጋሮቻቸውን አሰተባብረው ያደረጓቸው የጦር ልምምዶች በወታደሮችም ሆነ በጦር መሳሪያዎች አይነትና ብዛት ካለፈው አመት ከፍ ያሉ መሆናቸውም ውጥረቱ የተካረረ እንደነበር ያሳያል።