የአለማችን ውዷ ላም 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ወጥቶላታል
የነጯና ምርጥ ዝርያ ድቅሏ ላም ሲሶ ባለቤትነት በጨረታ በ1 ነጥብ 44 ሚሊየን ዶላር ተሽጧል
በአለማችን “ኔሎሬ” የተሰኙት የላም ዝርያዎች እጅግ ተፈላጊና ውድ ናቸው
የ4 አመት ተኩል እድሜ ያላት “ቫቲና 19 ማራ ኢሞቭስ” የአለማችን ውዷ ላም ሆናለች።
የዚህች ላም ሲሶው ባለቤትነት በቅርቡ በብራዙሏ አራንዱ ከተማ በ1 ነጥብ 44 ሚሊየን ዶላር ተሽጧል።
ይህም አጠቃላይ ዋጋዋን 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር እንደሚያደርሰው ነው የተነገረው።
“ኔሎሬ” የተሰኘው ዝርያ ድቅል የሆነችው ይህቺ ነጭ ላም ባለፈው አመትም የአለማችን ውዷ ላም ክብረወሰንን መያዝ መቻሏ ይታወሳል።
ባለፈው አመት የላሟ ግማሽ የባለቤትነት ዋጋ በጨረታ 800 ሺህ ዶላር ማውጣቱን ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው አውስቷል።
“ኔሎሬ” የተሰኙት የላም ዝርያዎች በአለማችን እጅግ ውድ ሲሆኑ ተፈላጊነታቸው በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።
በነጭ እና ለስላሳ ቆዳቸው የሚታወቁት የ”ኔሎሬ” ላም ዝርያዎች በበርሃማ አካባቢዎች ሙቀትን የመቋቋም አቅማቸው ከፍ ያለ ነው።
በጥቂት መኖ ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉ ሲሆን፥ ለበሽታ ተጋላጭነታቸ እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑ ይነገራል።
ቆዳቸውም ደም የሚመጡ ደቂቅ ተህዋሲያን ወደ ሰውነታቸው ዘልቀው እንዲገቢ የሚፈቅድ አለመሆኑ ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
ስያሜያቸው ከህንዷ አንድራ ፕራዴሽ አካባቢ የተወሰደው የ”ኔሎሬ” ላም ዝርያዎች በአለማችን ውድ ከሆኑ የላም አይነቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
በደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ብራዚል ብቻ ከ167 ሚሊየን በላይ ነጭና ውዶቹ ላሞች አሉ።