በእድሜ ባለጠጋዎች መኖሪያዋ ደሴት የሚዘወተረው "እድሜ ቀጣዩ ወጥ"
የግሪኳ ኢካሪያ ደሴት ነዋሪዎች ከ100 አመት በላይ እድሜ ያላቸው በርካታ ሰዎች መኖሪያ ናት
የደሴቷ ነዋሪዎች የተለያዩ አትክልትና ጥራጥሬዎችን በመጠቀም የሚያዘጋጁት ወጥ የረጅም እድሜያቸው ሚስጢር መሆኑን ይናገራሉ
የግሪኳ አካሪያ ደሴት በአለማችን ሰዎች ረጅም እድሜ ይኖሩባቸዋል ተብለው ከተለዩ አምስት "ሰማያዊ ዞኖች" ውስጥ አንዷ ናት።
ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች በቋሚነት የሚኖሩባት ደሴት ውስጥ ስር የሰደደና ገዳይ በሽታ እምብዛም አይታይም።
አይካሪያኖች አትክልትና ፍራፍሬ ያዘወትራሉ፤ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ትስስራቸውም ያስቀናል ይባልላቸዋል።
የደሴቷ ነዋሪዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግን ባህል ማድረጋቸውና ቀን ላይ አጭር ሸለብታ (ናፕ) በመውሰድ በንቃት ወደ ስራ መመለሳቸውም ጤናማና ረጅም ህይወት እንዲኖሩ አግዟቸዋል።
ከደሴቷ ነዋሪዎች ውስጥ ከሲሶ በላዩ እድሜያቸው ከ90 አመት በላይ ነው፤ አይካሪያኖች ከአሜሪካውያን በአስር እጥፍ የበለጠ ከ100 አመት በላይ የመኖር እድል እንዳላቸውም ጥናቶች አሳይተዋል።
ከላይ የተጠቀሱት የአመጋገብና የኑሮ ዘይቤያቸው ለረጅም እድሜያቸው አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይነገራል። ዋነኛው ጉዳይ ግን "እድሜ ቀጣዩ ወጥ" መሆኑን ይናገራሉ።
ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ነጭ ሽንኩርት፣ እንስላል እና ጥቁር ነጠብጣብ ያለው አተር "የእድሜ ቀጣዩ ወጥ" ግብአቶች ናቸው።
የስነምግብ ባለሙያዋ ሄለን ቤል ከሚረር ጋር ባደረጉት ቆይታ የአይካሪያኖች ልዩ ወጥ በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
"በርካታ አትክልቶች የሚገባበት የአይካሪያኖች ወጥ በፋይበርና ሌሎች ጠቃሚ ንጥረነገሮች የበለጸገ ነው፤ ጥቁር አይን ያላቸው አተሮች በአይረንና ሌሎች ማዕድናት የበለጸጉ ከመሆናቸው ባሻገር ለረጅም ጊዜ የመጥገብ ስሜትን ይፈጥራሉ፤ ይህም ጤናማ የምግብ ኡደት ስርአት እንዲኖር ያደርጋል" ነው ያሉት።
"እድሜ ቀጣዩ ወጥ" ሲሰራ ቀይ ሽንኩርት፣ የእንስላል አቃፊ ግንድ እና ነጭ ሽንኩርቱ በቅድሚያ በደምብ እስኪለሰልሱ ድረስ ከበሰሉ በኋላ አተሩ ይጨመራል። ከዚያም የቲማቲም ድልህ ተጨምሮ አተሩን እስኪሸፍነው ድረስ ውሃ ይከለሳል። ከ40 ደቂቃ እስከ 1 ስአት ከበሰለ በኋላ ጥቂት ጨው እና የተፈጨ እንስላል ተጨምሮበት ዝግጅቱ ይጠናቀቃል።
ለአይካሪያኖች የእድሜ መርዘም ትልቅ ድርሻ አለው የተባለው ወጥ አንዱ ግብአት የሆነው ባለጥቁር አይኑ አተር ክብደትን ለመቀነስ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የስነምግብ ባለሙያዋ ይገልጻሉ።
ተአምረኛ ነው የተባለው ወጥ ብቸኛው የአይካሪያኖች የረጅም እድሜ ሚስጢር እንዳልሆነ በማከል።
ከግሪኳ ደሴት ነዋሪዎች አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የህይወት ልምዶችን መቀሰም ይገባልም ነው ያሉት።