የአለማችን የእድሜ ባለጸጋ ቶሚኮ ኢቶካ በ116 አመታቸው አረፉ
ጃፓናዊቷ ኢቶካ አንደኛው የአለም ጦርነት ከመጀመሩ ከስድስት አመት በፊት ነበር የተወለዱት
የኢቶካን ማረፍ ተከትሎ ብራዚላዊቷ ኢናህ ካናባሮ የአለማችን የእድሜ ባለጸጋ ክብርን ይይዛሉ
ጃፓናዊቷ የአለማችን የእድሜ ባለጸጋ ቶሚኮ ኢቶካ በ116 አመታቸው ህይወታቸው አልፏል።
ኢቶካ በዮጎ ግዛት አሺያ በተባለች ከተማ በሚኖሩበት የአዛውንቶች መንከባከቢያ ቤት ማረፋቸውን የጃፓን ባለስልጣናትን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
"ወይዘሮ ኢቶካ በረጅም ህይወታቸው ጽናት እና ተስፋን ሰጥተውናል" ብለዋል ከእርሳቸው በ89 አመት የሚያንሰው የአሺያ ከተማ ከንቲባ ዮሱኬ ታካሺማ።
ኢቶካ የተወለዱት አንደኛው የአለም ጦርነት ከመጀመሩ ከስድስት አመት በፊት በ1908 ነበር። የተወለዱበት አመት የ"ፎርድ ሞዴል ቲ" መኪናዎች ለአሜሪካ ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡበትም እንደነበር ተገልጿል።
የአለማችን ዋና ዋና ክስተቶችን የተመለከቱት ቶሚኮ ኢቶካ በህይወት ያሉ የምድራችን የእድሜ ባለጸጋ ተብለው በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸው የሰፈረው በመስከረም 2024 ነው።
ስፔናዊቷ ማሪያ ባራንያስ ሞሬራ በነሃሴ ወር 2024 በ117 አመታቸው ማረፋቸውም በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስማቸው እንዲያርፍ ምክንያት ሆኗል።
በ20 አመታቸው አግብተው አራት ልጆችን የወለዱት ኢቶካ አለማችን ያሳለፈቻቸው ጦርነቶችና ወረርሽኞች ብሎም ፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ሁሉ አይተዋል።
ባላቸውን በ1979 ካጡ በኋላ በናራ ከተማ አራት ልጆቻቸውን ብታቸውን ያሳደጉ ሲሆን፥ ሁለት ልጆቻቸውን በሞት ቢነጠቁም አምስት የልጅ ልጆችን ማየት ችለዋል።
ተማሪ እያሉ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች የነበሩት ኢቶካ 3 ሺህ 67 ሜትር ከፍታ ያለውን የኦንቴክ ተራራ ሁለት ጊዜ ወጥተዋል።
እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ሙዝ እና በጃፓናውያን የሚወደደው ከወተት የሚዘጋጅ መጠጥ (ካልፒስ) ማዘውተራቸው ረጅም እድሜ ለመቆየታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረው ነበር።
ጃፓን እንደ ኢቶካ ያሉ በርካታ ዜጎች የሚኖሩባት ሀገር ናት። እስከ መስከረም 2024 ባለው መረጃ በሀገሪቱ ከ95 ሺህ በላይ እድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፤ ከዚህ ውስጥ 88 በመቶው ሴቶች ናቸው።
ከሩቅ ምስራቋ ሀገር 124 ሚሊየን ህዝብ ሲሶው 65 እና ከዚያ በላይ እድሜ ያለው ሲሆን፥ የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር በየአመቱ ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ ይገኛል።
ጃፓናዊቷ ኢቶካ ከተወለዱ ከ16 ቀናት በኋላ ይህቺን ምድር የተቀላቀሉት ብራዚላዊቷ ኢናህ ካናባሮ ሉካስ የአለማችን በህይወት ያሉ የእድሜ ባለጠጋ ክብርን እንደሚይዙ ይጠበቃል።