የአለማችን በእድሜ አዛውንቶቹ ጥንዶች በመቶ አመታቸው ተሞሽረዋል
ፍቅር አያረጅም የሚሉት አዛውንቶች “እድሜ በፈጣሪ እጅ ነው” በሚል በአድሜያቸው ማምሻ አዲስ ሙሽራ ሆነዋል
ጥንዶቹ የፍቅር ግንኙነታቸውን የጀመሩት በአረጋውያን ማቆያ ሲሆን በእድሜ ትልቁ አዲስ ሙሸራ በመባልም በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሰፍረዋል
የ102 ዓመቷ ማርጆሪ ፊተርማን እና የ100 ዓመቱ በርኒ ሊትማን በእድሜ ማምሻቸው በአሜሪካ ፊላደልፊያ በሚገኝው የአረጋውን ማቆያ ሲገቡ የህይወት ጉዟቸው የተገባደደ ይመስል ነበር፡፡
ነገር ግን በምድር የቆዩባቸው ጊዚያት ሲደመሩ የ202 አመት እድሜ ያላቸው የዓለማችን እድሜ ጠገቦቹ አዲስ ተጋቢዎች በአረጋውያን ማቆያ በፍቅር ይወድቃሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም፡፡
ምንም እንኳን ሁለቱም ከዓመታት በፊት በተመሳሳይ ጊዜ የፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩ ቢሆኑም የቀደመ እውቅና ሳይኖራቸው ህይወት በራሷ አጋጣሚ አዟዙራ አገጣጥማቸዋለች፡፡
በርኒ ሊትማን በአረጋውያን ማቆያ ውስጥ በአልባሳት ውድድር ፕሮግራም ላይ አይናቸውን የጣሉባትን ማርጆሪን ለማፍቀር የእድሜያቸው መግፋት አልገደባቸውም፡፡
በተመሳሳይ ቀን ሁለቱ ጥንዶች የፍቅር ቀጠሮ አድርገው ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ልክ እንደወጣት በፍቅር ከነፉ፡፡
ጥንዶቹ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የነበራቸው መዋደድ እና መተሳሰብ በአረጋውያን ማቆያ ውስጥ ለብዙዎች የተስፋ ጮራን የፈነጠቀ ፣ በብዙዎችም ውስጥ የህይወት መቀጠለን ያስተማረ እና ነፍስ የዘራ ፍቅር ሲሉ ወዳጆቻቸው ይገልጹታል፡፡
ማርጆሪ እና በርኒ ለ9 አመታት በፍቅር ከቆዩ በኋላ ለፍቅራቸው የማይፋቅ ማሕተም ለመምታት በማሰብ በትዳር መጣመርን መርጠው ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ተሞሽረዋል፡፡
“እድሜ በፈጣሪ እጅ ነው” የሚሉት የ100 አመቱ በርኒ “ለመሞት አንድም ቀን ቢቀረን ለደስታችን ቀጠሮ መስጠቱን ባለመፈለግ ለመጋባት ወስነናል” ሲሉ ተናግረዋል
የበርኒ የልጅ ልጅ ብዙዎች ሞታቸውን በመጠባበቅ በሚኖሩበት እድሜ ላይ በልባቸው ውስጥ የተቀጣጠለው የፍቅር እሳት ለዚህ ስላበቃቸው ቤተሳቦቻቸው ደስተኛ መሆናቸውን ትናግራለች፡፡
የፍቅር ግንኙነታቸውን የሚያውቁ ሰዎች ከሚገኙበት የእድሜ ሁኔታ አንጻር በፍቅር መቆየትን እንጂ በትዳር መጣመርን ያስባሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም፡፡
ከዚህ ቀደም በነባራቸው ህይወት ሁለቱም ለ60 አመታት እና ከዛ በላይ ለሆነ ጊዜ ከአጋሮቻቸው ጋር በትዳር ኖረዋል፡፡
በዙዎች በፍቅር ታምነው ረጅም አመታትን ለመቆየት ፈተና በሆነበት በዚህ ጊዜ በፍቅር አያረጅም ቢሂል ለመዋደድ እና በፍቅር ለመኖር የእድሜ ገደብ ያላስቆማቸው ጥንዶቹ በማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገርያ ሆነዋል፡፡
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብም በእድሜ ትላልቆቹ አዲስ ሙሽሮች በሚል እውቅናን ሰጥቷቸዋል፡፡