በቀጣዮቹ 8 ሳምንታት ከአውሮፓ ህዝብ ግማሽ ያህሉ በኦሚክሮን ሊያዝ ይችላል ተባለ
በየሳምንቱ 1 በመቶ የሚሆነው ህዝባቸው በቫይረሱ እየተያዘ መሆኑን 26 የአውሮፓ ሃገራት አሳውቀዋል
ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በመላው አውሮፓ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል
እስከ መጪው መጋቢት ከአጠቃላዩ የአውሮፓ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በኦሚክሮን ቫይረስ ሊያዙ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ከፍተኛ የመተላለፍ አቅም እንዳለው የተነገረለት አዲሰ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መንግስታት በሮቻቸውን እንዲዘጉና ለዜጎቻቸው የማጠናከሪያ ክትባቶችን እንዲሰጡ እያስገደደ ነው ተብሏል፡፡
አውሮፓ አሁንም በወረርሽኙ ማዕከልነት እየተጠቀሰ ነው፡፡ ወደ ሆስፒታሎች የሚገቡና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነውም ተብሏል፡፡
ወረርሽኙ በዚህ ፍጥነቱ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የአውሮፓን ህዝብ ሊያጠቃ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ይህ ከ6-8 ባልበለጡ ቀጣይ ሳምንታት ውስጥ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው እንደ የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዳይሬክተር ሃንስ ክሉዥ ገለጻ፡፡
ዳይሬክተሩ በአውሮፓ እና በማዕከላዊ እስያ የሚገኙ 53 ሃገራትን የጤና ጉዳይ ይከታተላሉ፡፡ ኦሚክሮን ከ53ቱ በ50ዎቹ ሃገራት ሪፖርት ተደርጓል፡፡
በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ከ7 ሚሊዮን በላይ ኬዞች በመላው አውሮፓ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ይህ ከቀደሙት 2 ሳምንታት የእጥፍ እጥፍ ነው፡፡
እስከ ትናንት ሰኞ ድረስ 26 የአውሮፓ ሃገራት በየሳምንቱ 1 በመቶ የሚሆነው ህዝባቸው በቫይረሱ እየተያዘ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ተከትሎ በርካታ በረራዎች መሰረዛቸው ይታወሳል፡፡
የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ከሞተ ድፍን 2 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚያ ወዲህ ወደ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
የቫይረሱ መነሻ ነች በሚል የምትጠቀሰው ቻይና የአዲሱን ዝርያ ስርጭት ለመግታት በሚል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን እንቅስቃሴ እየገደበች መሆኑም ተሰምቷል፡፡