የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “የሩስያ አውዳሚ ጦርነት የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው” አሉ
ዘለንስኪ፤ ህዳር 19 የሚያበቃው የእህል ኤክስፖርት ስምምነት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምም ጠይቀዋል
በሩሲያ የነዳጅ ምርቶች ላይ የዋጋ ገደብ እንዲደረግም ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጠይቀዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ “የሩስያ አውዳሚ ጦርነት የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው” አሉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በባሊ እየተካሄደ ባለው የቡድን-20 ስብሰባ ላይ ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር ላይ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ዘለንስኪ አሜሪካንና የቻይና መሪዎች እንዲሁም ሩሲያን የወከሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርገይ ላቭሮቭ እየተሳተፉበት ባለው የኢንዶኔዢያው ጉባኤ ላይ"የበርካቶችን ህይወት ለማታደግ፤ የሩሲያ አውዳሚ ጦርነት መቆም ያለበት ጊዜ አሁን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የዩክሬኑ መሪ በተባበሩት መንግስታት እና በቱርኪ አሸማጋይነት የተያዘው ህዳር 19 የሚያበቃው የእህል ስምምነት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምም ጠይቀዋል።
"ጦርነቱ ምንም ይሁን ምን - የእህል ኤክስፖርት ስምምነቱ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘም አለበት" ብለዋል።
ዩክሬን ከዓለም ምርጥ እህል አምራቾች አንዷ ብትሆነም በጦርነቱ ምክንያት በሐምሌ ወር ስምምነቱ እስኪደረስ ድረስ 20 ሚሊዮን ቶን እህል ከወደቦቿ እንዳታንቀሳቅው ተገዳ እንደነበር ይታወሳል።
የዩክሬን መሪም ሩሲያን "ቀዝቃዛውን ወደ መሳሪያነት ለመቀየር ሙከራ አድርጋለች" በማለት ከመጪው ክረምት በፊት ቁልፍ በሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከሰዋል።
በተጨማሪም ዘለንስኪ “ ሞስኮ የኢነርጂ ሃብቶች እንደ ጦር መሳሪያ እንዳትጠቀም” በሩሲያ የነዳጅ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ገደብ ለማድረግ በአሜሪካ የሚመራውና የሚደረገው ግፊት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
"ሩሲያ ዩክሬንን፣ አውሮፓን እና በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም የሃይል ተጠቃሚዎችን ትንበያ እና የዋጋ መረጋጋትን ለማሳጣት እየሞከረች ከሆነ ለዚህ መልሱ ለሩሲያ የወጪ ንግድ ዋጋ መገደብ መሆን አለበት" ሲሉም ተደምጠዋል ፕሬዝዳንቱ።