ልዩልዩ
የመጀመሪያ ነው የተባለለት አጭር የጽሁፍ መልዕክት በ120 ሺ ዶላር ተሸጠ
ከ30 ዓመታት በፊት ነበር እንግሊዝ ለሚገኝ የቮዳፎን ስራ አስኪያጅ የተላከው
መልዕክቱ 'Merry Christmas' የሚል ነበር
የመጀመሪያው የ“እንኳን አደረሳችሁ” አጭር የጽሁፍ መልዕክት በ120 ሺ ዶላር ተሸጠ፡፡
መልዕክቱ ትናንት ማክሰኞ ነው በፈረንሳይ ፓሪስ ለጨረታ ቀርቦ በ120 ሺ ዶላር የተሸጠው፡፡
ሻጩ ደግሞ ግዙፉ የእንግሊዝ የቴሌኮም ኩባንያ ቮዳፎን ነው፡፡ ቮዳፎን ከ30 ዓመታት በፊት እንግሊዝ ለነበረ ስራ አስኪያጁ የተላከውን አጭር የጽሁፍ መልዕክት ነው በጨረታ አወዳድሮ የሸጠው፡፡
መልዕክቱ በፈረንጆቹ ታህሳስ 3/1992 ነው ከጀርመን ሃኖቨር በወቅቱ እንግሊዝ ይገኝ ለነበረው የቮዳፎን ስራ አስኪያጅ የተላከው፡፡
ላኪው ኔይል ፓፕወርዝ ይባላል፤ የኩባንያው የኮምፒውተር መሃንዲስ ነው፡፡
ፓፕወርዝ 'Merry Christmas' ሲል ወደ አለቃው የእጅ ስልክ ልኳል፡፡ ስራ አስኪያጁም 'ኦርቢቴል' በተባለና በወቅቱ ዝነኛ በነበረ ስልክ ከኮምፒውተር የተላከውን መልዕክት ተቀብሏል፡፡
በወቅቱ የነበሩ ስልኮች መልዕክት ለመጻፍ የሚያስችል የፊደል ቁልፍ 'ኪቦርድ' አልነበራቸውም፡፡
ይህ መልዕክትም ነው ትናንት ማክሰኞ በፓሪስ ለጨረታ ቀርቦ በ120 ሺ ዶላር የተሸጠው፡፡ በዲጂታል መልክ የተዘጋጀው መልዕክት ጨረታ በኦን ላይን ነበር የተካሄደው፡፡