400 ሚሊየን ሰዎች የሚሳተፉበት የአለም ግዙፍ ሀይማኖታዊ ፌስቲቫል በህንድ እየተካሄደ ነው
“ማሃ ኩምብህ ሜላ” የተሰኘው ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓት በሂንዱ እምነት ተከታዮች ዘንድ በ12 አመት አንዴ የሚካሄድ ነው
ለዝግጅት 800 ሚሊየን ዶላር የሚያስወጣው ክብረ በዓል እስከ 35 ቢሊየን ዶላር ድረስ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ እንደሚኖረው ይነገራል
በህንድ ሰሜናዊ ግዛት ኡታር ፕራዴሽ የአለም ትልቁ ሀይማኖታዊ ስነስርአትን ለመታደም በሚልዮን የሚቆጠሩ የሂንዱ ዕምነት ምእመናን ወደ ስፍራው እየተመሙ ነው፡፡
በፕራያግራጅ ከተማ ምዕመናን “ኃጢአታቸውን ለማንጻት እና መንፈሳዊ ነፃነትን ለመቀዳጀት” የሶስት ቅዱስ ወንዞች መገናኛ በሆነው በትሪቪኒ ሳንጋም ወንዝ ላይ የእጥበት (ጥምቀት) ስነስርት ያካሄዳሉ።
በሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ፣ ፕራያግራጅ ከተማ በወንዝ ዳርቻ ላይ “በማሃ ኩምብህ ሜላ” በዓል ላይ 400 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሀይማኖታዊ ስነስርአቱ በሂንዱ አፈ ታሪክ መሰረት ሰይጣን እና አማልክት ያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ በፕራያግራጅ፣ ናሺክ፣ ሃሪድዋር እና ኡጃይን ውስጥ የሚገኙ ወንዞችን የፈጠሩ መንፈሳዊ ውሀዎች የተገኙባቸው አካባቢዎች ናቸው በሚል ነው የጥምቀት ስርአቱ የሚካሄደው፡፡
በዓሉ “ሳዱስ” የተባሉት የእምነቱ ሰዎች በስፋት የሚሳተፉበት ሲሆን የዕምነቱ ቅዱሳን እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሳዱሶች አለማዊ ህይወትን እና ሸቀጦችን የተው በድሬድ ጸጉራቸው እና ሰውነታቸው ላይ በሚቀቡት ነጭ ቀለም የሚታወቁ ናቸው፡፡
ከሀይማታዊ ስነ ስርዓት ተሻግሮ ትውፊታዊ ቀለም የተላበሰው ስነ ስርዓት በ2017 በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት በዩኒስኮ ተመዝግቧል፡፡
የዘንድሮው ፌስቲቫል አዘጋጅ የሆነችው የ6ሚሊየን ዜጎች መኖሪያ የሆነችውን ፕራያግራጅ ከተማ ለበዓሉ ለማሰናዳት አመታትን የፈጀ ዝግጅት እና በሚሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ተደርጓል፡፡
ለዚህ አመት የወጣው ወጪ 800 ሚሊየን ዶላር እንደሚጠጋ የዘገበው ሮይተርስ ክብረ በዓሉ ከ30-35 ቢሊየን ዶላር ኢኮኖሚያዊ እድገት አበርክቶ ይኖረዋል ብሏል፡፡
160 ድንኳኖች 7500 የእግር ኳስ ሜዳዎችን በሚሸፍን ስፍራ ላይ ተዘርግተዋል ፣ 150 ሺህ መጸዳጃ ቤቶች እና 1249 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመጠጥ ውሃ ቧንቧ መስመር ተዘርግቷል።
በሀይማኖታዊ በዓለት በሚፈጠር መጨናነቅ ተደጋጋሚ አደጋዎችን በምታስተናግደው ህንድ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ የከተማዋ ፖሊሶች ሰፊ ዝግጅቶችን ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ባለፈም 50 ሺህ ፖሊሶች እና በጎ ፈቃደኞች በአሉን ለማስተባበር ተሰማርተዋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን በባቡር ወደ ክልሉ ይጓዛሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ ባለስልጣናት 3 ሺህ ልዩ ባቡሮችን እና 13 ሺ የባቡር አገልግሎቶችን ጨምረዋል።
11 አዳዲስ የመንገድ ኮሪደሮች ፣ 550 አውቶብሶች ፣ 14 የፍጥነት መንገዶች እና ሌሎችም ግዛቱን በዓሉ ከሚከበርበት ከተማ ጋር የሚያገናኙ መሰረተ ልማቶች ተሟልተዋል፡፡