አለም አቀፍ የመኪና አምራቾች እና የገበያ ድርሻቸው ምን ይመስላል?
አሜሪካ ጀርመን እና ቻይና በአለም አቀፍ የመኪና ገበያ ድርሻ ውስጥ ከፍተኛ ፉክክር እደረጉ ነው
የመኪና ሽያጭ ገበያው ከ2.129 ትሪሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ነው
የሰውን ልጅ ህይወት ካቀለሉ እና የእለት ከዕለት እንቅስቃሴውን እጅግ ፈጣን ካደረጉ የፈጠራ ውጤቶች መካከል መኪና አንዱ ነው።
መኪኖች ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ከመጓጓዣነት አልፈው በንብረትነት፣ የቅንጡ እና የሀብት ኑሮ ማሳያ፣ እንዲሁም የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች መፎካከርያ አውድ ሆነው ቆይተዋል።
በአለም አቀፍ ገበያ ሰፊ ተፈላጊነት እና የገበያ ድርሻ ባላቸው የመኪና አምራቾች መካከል የሚደረገው ፉክክርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።
ይህ ፉክክር ምቾትን፣ ፍጥነትን፣ የደህንነት ዋስትናዎችን፣ ውብትን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መሰረት አድረጎ በገበያ ውስጥ ላቅ ያለ ድርሻን እና ተቀባይነትን ለማግኝት በሚደረግ እሽቅድድም ይገለጻል።
የተለያዩ አለም አቀፍ ኩባንያዎችን የገበያ ድርሻ እና ተቋማዊ ቁመና ዝርዝር የሚያወጣው “ካምፓኒስ ማርኬት ካፕ” በአለም አቀፍ ደረጃ ዋና ዋና የሚባሉ 63 የመኪና አምራች ድርጅቶች አጠቃላይ የገበያ ድርሻ 2.129 እንደሚገመት አመላክቷል።
የጀርመን ፣ አሜሪካ ፣ ቻይና ፣ ጃፓን እና የጣሊያን መኪና አምራች ኩባንያዎች በዚህ ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ፉክክርን እያደረጉ የሚገኙ ናቸው።
ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ካላቸው 10 የመኪና አምራች ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ ጀርመን አራት ኩባንያዎችን በማስቀመጥ ቀዳሚዋ ስትሆን፤ አሜሪካ 3 ፣ ቻይና ፣ ጃፓን እና ጣሊያን እያንዳንዳቸው አንድ ኩባንያን ማካተት ችለዋል።
የአለማችን ቁጥር አንድ ባላሀብት ኢለን መስክ ድርጅት የሆነው ቴስላ 1.02 ትሪሊየን ዶላር የገበያ ድርሻ በመያዝ በአንደኛ ደረጃ ይገኛል።
ስመ ጥሩ የጃፓን ኩባንያ ቶዮታ በ227 ቢሊየን ዶላር ሲከተል ቢዋይዲ ፣ ፌራሪ እና ጄነራልሞተርስ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።