አለማቀፉ የእባብ ቀን እየተከበረ ነው
ቀኑ አስፈሪዎቹ ተሳቢ እንስሳት ለስነምህዳር ሚዛን መጠበቅ ያላቸው ድርሻ እንዲታወቅና ልማዳዊ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ለማረም ነው የሚከበረው
በአለማችን ከ3 ሺህ በላይ የእባብ ዝርያዎች ቢኖሩም ሰዎችን መግደል የሚችሉት 7 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው
ስለእባብ ስናስብ አስቀድሞ ወደአዕምሯችን የሚመጣው ተናድፎ ገዳይነቱ ነው።
ተደብቆ የሚያጠቃንን አካል “እባብ” የሚል ተቀጽላ የመስጠት ልማድም አለን።
የእባብን ተፈጥሮና ባህሪ የሚያጠኑት ተመራማሪዎች ግን ያለጥፋቱ ወንጀለኛ የተደረገ ተሳቢ እንሰሳ ነው ይላሉ።
ሊታይ በማይቻልበት ስፍራ የሚኖረው ራሱን ለማዳን መሆኑን በመጥቀስም ሰላም ፈላጊነቱን አጉልተው ይጽፋሉ።
ከ15 እስከ 30 አመት እድሜ ያላቸው እባቦች ጆሮ ስለሌላቸው የተጣራ ድምጽ አይሰሙም። ይሁን እንጂ ከምላሳቸው ላይ በተጣበቀ አካል የሰዎችን እንቅስቃሴም ሆነ ማንኛውም አካል የሚፈጥረውን እርግብግቢት መረዳት ይችላሉ።
በአለማችን ከ3 ሺህ በላይ የእባብ ዝርያዎች እንዳሉ ይነገራል። ከእነዚህ የእባብ ዝርያዎች ውስጥ ሰዎችን ነድፈው ሊገድሉ ወይም ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉት 200 (7 በመቶ) ብቻ ናቸው ይላል የናሽናል ጂኦግራፊ መረጃ።
በክፋት የተሳሉት ተሳቢ እንሰሳት ፋይዳቸው ተዘንግቷል ያሉ ተመራማሪዎች የአለም የእባብ ቀን በየአመቱ ሃምሌ 16 እንዲከበር ማድረግ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል።
የሚፈሩት እባቦች እንደ አይጥ ያሉ አነስተኛ ነፍሳትን በመመገብ የስነምህዳር ሚዛንን ያስጠብቃሉ። ለሌሎች ነፍሳትም በምግብነት ይውላሉ።
ባለሙያዎች እባቦች የሚገኙበት አካባቢ ሚዛናዊና ጤናማ ስነምህዳርን ያመላክታል የሚሉ ሲሆን፥ ለአጠቃላይ የስነምህዳር ምርምራቸውም ግብአት ያደርጉታል።
መርዝ የሚረጩ እባቦች ጭምር ለዘመናዊ ህክምና እድገት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ነው የሚነገረው።
የእባብ መርዝ ለደም ግፊት፣ ደም መርጋት እና ሌሎች በሽታዎች መድሃኒቶችን ለመስራት እንደሚውልም የህንዱ ኤንዲቲቪ ዘገባ አመላክቷል።