የዓለም ንግድ ድርጅት የዓለም ንግድ መጠን በእጅጉ እንደሚቀንስ በትንበያው አመለከተ
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ “የ2023 ስዕል በከፍተኛ ሁኔታ ጨልሟል”ብለዋል
በ2023 የሚኖረው ዓለም አቀፍ የንግድ መጠን በ1 በመቶ ብቻ እንደሚገደብ የዓለም ንግድ ድርጅት ጥናት ያመለክታል
የዓለም ንግድ ድርጅት የዓለም ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ በ2023 የሚኖረው የዓለም ንግድ መጠን በእጅጉ እንደሚቀንስ በትንበያው አመላከተ፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ “ዛሬ የዓለም ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ገጥመውታል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅት ኢኮኖሚስቶች ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በዚህ አመት የንግድ መጠኑ በ3 ነጥብ 5 በመቶ የሚያድግ ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም ከተጠበቀው ትንሽ ከፍ ያለ ነው ተብሏል።
ጥናቱ በ2023 የሚኖረው ዓለም አቀፍ የንግድ መጠን በአንድ በመቶ ብቻ እንደሚገደብና ይህም በሚያዝያ ወር ከነበረው የ3.4 በመቶ ትንበያ በእጅጉ እንደሚቀንስ አመላክቷል፡፡
በዚህ ከፍተኛ ስጋት ያደረባቸው ዋና ዳይሬክተሯ “የ2023 ስዕል በከፍተኛ ሁኔታ ጨልሟል”ብለዋል፡፡
ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ በቅረቡ በጄኔቫ በተሳለጠው ዓለም አቀፉ የንግድ ፎረም መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር “ወደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ድቀት እየገባን ያለ ይመስለኛል፤ እናም በተመሳሳይ ጊዜ ስለ ማገገም ማሰብ መጀመር አለብን ፤እድገትን መመለስ አለብን” ሲሉ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
በዩክሬን ያለው የሩሲያ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ የምግብ ዋጋ እና የኢነርጂ ድንጋጤ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዘዝ ለዓለም የኢኮኖሚ ውድቀት ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ እድገትን ለማነቃቃት ስር ነቀል ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል ።
የንግድ ትንበያ ቁጥሮች የሚያመላክቱት ነገሮች ጥሩ እንዳመይሆኑ ነውም ብለዋል ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ ፡፡
አክለውም “የደህንነት ፣ የአየር ንብረት፣ የኢነርጂ ፣ የምግብ ዋጋ መናር ስጋቶች አሉብን ፣ስለዚህም እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባሉበት እንደተለመደው ቢዝነስ ለመስራት አንችልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የናይጄሪያ ፋይናንስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ “ማዕከላዊ ባንኮች የወለድ ምጣኔን ከማጥበቅ እና ከመጨመር በስተቀር ብዙ ምርጫ የላቸውም።
ነገር ግን በታዳጊ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ የሚያስከትሉት መዘዞች በጣም ከባድ ናቸው ምክንያቱም እነሱም የወለድ ምጣኔን ይጨምራሉ”ማለታቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ኦኮንጆ-ኢዌላ፤ ዋነኛ ትኩረታቸው የምግብ ዋስትናን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል እና ከዚያም የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
“የሚያስጨንቀኝ በቂ ምግብ ካለማግኘት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው” ነበር ብለዋል፡፡