ብራዚሊያዊቷ ሊቪያ በደቡብ አሜሪካ ያለ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ባለቤት ናት
የዩንቨርሲቲ ተማሪዋ ወጣቷ ቢሊየነር ሊቪያ ቮጅት፡፡
ብራዚሊያዊቷ ሊቪያ ቮጅት በዓለማችን ካሉ በእድሜ ትንሿ ባለጸጋ በሚል መመዝገቧን ፎርብስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ሊቪያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት ባለቤት ስትሆን በደቡብ አሜሪካ ዋነኛ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት እና በመሸጥ የሚታወቀው ደብሊውኢጂ ኩባንያ አብዛኛው ድርሻ ካላቸው ግለሰቦች መካከል ቀዳሚዋ ነች ተብሏል፡፡
የብራዚል ዜግነት ያላት ይህች ወጣት ቢሊየነር የዓለማችን ወጣት ቢሊየነር የሚለውን ደረጃ የያዘችው በሁለት ወር ከሚበልጣት ክሌመንት ቬቺዮ መረከቧ ተገልጿል፡፡
ይህች ወጣት አሁን ያላትን ሀብት ከቤተሰቦቿ እንደወረሰችው የተገለጸ ሲሆን ኩባንያው በ10 ሀገራት ፋብሪካዎች ሲኖሩት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢም አለው ተብሏል፡፡
ወጣቷ ባለጸጋ አሁን ላይ በዚህ ድርጅት ውስጥ ምንም አይነት ሀላፊነት የላትም የተባለ ሲሆን የዩንቨርሲቲ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደሆነች ተገልጿል፡፡
በዓለማችን ካሉ ወጣት ቢሊየነሮች ውስጥ ከሊቪያ በመቀጠል የ25 ዓመት እድሜ ያላት ዶራ የተሰኘችው እህቷ ከምርጥ 25 ቢሊየነሮች ውስጥ ስማቸው ተካቷል፡፡
ሌላኛው ጣልያናዊ የ19 ዓመቱ ክሌመንቲ ቫቺዮ እና ሉቻ ቫቺዮ እያንዳንዳቸው 4 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በመያዝ የዓለማችን ቀዳሚ ወጣት ባለጸጋዎች ናቸው፡፡
የሁለቱ ወንድማማቾች አባት መነጽሮችን ጨምሮ የአይን መዋቢያ ምርቶችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ባለቤት ናቸው፡፡
ሚስትሪ በመባል የሚታወቁት የ25 እና 27 ዓመት እድሜ ያላቸው አየርላንዳዊ ወንድማማቾች በ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ሀብት ከወጣት ባለጸጋዎች መካከል ተዘርዝረዋል፡፡
እነዚህ ወጣቶች መቀመጫውን ሕንድ ሞምባይ ያደረገው ታታ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሀይል ዘርፍ ባሉ ኢንቨስትመንቶች ዙሪያ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡