ሃውቲዎች በአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹ
የየመኑ ቡድን በቀይ ባህር በምትገኘው "ዩኤስኤስ ሃሪ ቱርማን" መርከብ ላይ 18 ሚሳኤሎችን መተኮሱን አስታውቋል

አሜሪካ ቅዳሜ እለት በየመን በፈጸመችው የአየር ጥቃት 53 ሰዎች መገደላቸውና 98 ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሃውቲ በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ።
ጥቃቱ 53 የመናውያን ለሞቱበት የቅዳሜው የአሜሪካ የአየር ድብደባ አጻፋ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።
በኢራን ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚታመነው ሃውቲ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በቀይ ባህር በምትገኘውና አውሮፕላን ተሸካሚዋ "ዩኤስኤስ ሃሪ ቱርማን" መርከብ ላይ በ24 ስአት ውስጥ ሁለት ጊዜ ጥቃት ማድረሱን ጠቁሟል።
ቡድኑ በመርከቧ ላይ ጥቃት ለማድረስ 18 ሚሳኤሎችና ድሮኖች መጠቀሙን ቢገልጽም ጉዳት ስለመድረሱ ያለው ነገር የለም ብሏል ፍራንስ 24 በዘገባው።
አሜሪካም በሃውቲዎች ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም።
በቅዳሜው የአሜሪካ የአየር ጥቃት ህይወታቸው ካለፈው የመናውያን ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ያስታወቀው ሃውቲዎች የሚቆጣጠሩት የጤና ሚኒስቴር፥ 93 ሰዎች መቁሰላቸውንም አመላክቷል።
የሃውቲ ቃል አቀባይ "አሜሪካ በሀገራችን ላይ የምታደርገውን ወረራ ለማስቆም የምንፈጽመው ጥቃት" ይቀጥላል ሲል በቴሌግራም ገጹ አስፍሯል።
የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ታጣቂ ቡድኑ በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ካላቆመ ከባድ ዋጋ ይከፍላል በማለት ዝቷል።
ከየመን የወጡ ዘገባዎች ዋሽንግተን በትናንትናው እለትም በሆዴይዳ በሚገኝ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ላይ እና በሃውቲዎች ከተያዘች ከአንድ አመት በላይ ባስቆጠረችው "ጋላክሲ ሌደር" መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አመላክተዋል።
የሃውቲዎች መሪ አብዱልማሊክ አል ሁቲ የመናውያን በዛሬው እለት በአደባባይ የአሜሪካን ጥቃት እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት በበኩሉ አሜሪካም ሆነች የየመኑ ሃውቲ ውጥረት ከሚያባብስ እርምጃ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ሃውቲዎች እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች አንስቶ ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን ለማሳየት በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ከ100 በላይ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
በቅርቡም እስራኤል ወደ ጋዛ የትኛውም ድጋፍ እንዳይገባ ማገዷን ተከትሎ የአራት ቀናት ቀነ ገደብ መስጠታቸውና ዳግም ጥቃት ማድረስ እንደሚጀምሩ መዛታቸውም አይዘነጋም።
ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከተመለሱ በኋላ በየመን የአየር ድብደባ እንዲፈጸም ያዘዙት እና ቁጭ ብለው ጥቃቱን የተመለከቱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃውቲዎችን "ሲኦል ይዘንብባችኋል" ሲሉ በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢራን ለቡድኑ የታደርገውን ድጋፍ እንድታቆምም ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።
የኢራን አቢዮታዊ ዘብ አዛዡ ሆሴን ሳላሚ "ኢራን ጦርነት አታውጅም፤ የትኛውም አካል ከገፋፍፋት ግን ተገቢ እና ወሳኝ ምላሽ ትሰጣለች" ብለዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስም አሜሪካ በየመን የምትፈጸመው የአየር ድብደባ "አለማቀፍ ህግን የጣሰ እና ሉአላዊነትን የተዳፈረ ነው" በሚል ለሃውቲ ድጋፉን ገልጿል።