በብሪታንያ መሀመድ የሚለው ስም ቁጥር አንድ የህጻናት ስም ሆነ
በብሪታንያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተወለዱ ህጻናት ውስጥ ከ4 ሺህ 600 በላይ ያህሉ ስማቸው መሀመድ ተብሎ ተመዝግቧል

ለዓመታት ለብዙ ህጻናት ይሰጥ የነበረው ስም ኖህ የሚለው ነበር
በብሪታንያ መሀመድ የሚለው ስም ቁጥር አንድ የህጻናት ስም ሆነ፡፡
ስም ከማህበራዊ ማንነት መገለጫዎች መካከል አንዱ ሲሆን ወላጆች ልጆቻቸውን ከማንነታቸው ጋር ተያያዥ የሆኑ እና ትርጉም የሚሰጡ ስሞችን ይሰጣሉ፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ወይም ሶሺዮሎጅስቶች እንደሚሉት ወላጆች የልጆቻቸውን ስም ለማውጣት ሀይማኖትን፣ ክስተቶችን አልያም እንደ አርአያ የሚያዩትን ሰው መሰረት በማድረግ ስም ይሰይማሉ፡፡
የብሪታንያ ብሔራዊ መረጃ ማዕከል ባወጣው መረጃ በ2023 ዓመት ውስጥ ከተወለዱ አጠቃይ ህጻናት ውስጥ መሀመድ የሚለው ስም የተሰጣቸው ህጻናት ቁጥር ከፍተኛው ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ከዚህ በፊት በብሪታንያ እና ዌልስ ለብዙ ህጻናት ይሰጥ የነበረው ስም ኖህ የሚለው ሲሆን አሁን ላይ በመሀመድ ተበልጧል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከመሀመድ እና ኖህ በመቀጠልም ኦሊቨር እና ጆርጅ ሶስተኛ እና አራተኛ ተወዳጅ የወንድ ህጻናት ስሞች ተብለው ተመዝግበዋልም ተብሏል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ በብሪታንያ 4 ሺህ 600 ህጻናት መሀመድ ተብለው እንዲጠሩ የተሰየሙ ሲሆን ከሴት ደግሞ ኦሊቪያ፣ አሜሊያ እና ኢስላ የሚሉት ስሞች ከአንድ እስከ ሶስተኛ ድረስ ያሉ ተወዳጅ ስሞች ሆነዋል፡፡
ሊላህ፣ ራያ፣ ሀዝል፣ ኤንዞ እና ጃክስ የተሰኙ ስሞች ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሪታንያ ተወዳጅነታቸው እየጨመሩ ከመጡ ስሞች መካከል ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በታዋቂ ሰዎች ስም የሚጠሩ ህጻናት ቁጥር እያደገ ነው የተባለ ሲሆን በተለይም ሚሌይ፣ ኤንድሪክ፣ ሮቢ፣ሪሀና፣ ኤሊሽ፣ ላና እና ኤልተን ስሞች ዋነኞቹ ሆነዋል፡፡