የኮሮና ክትባቶችን የባለቤትነት መብት በጊዜያዊነት ለማንሳት ስምምነት ላይ ተደረሰ
ስምምነቱ ከስድስት ወራት በኋላ ሊከለስ ይችላል ተብሏል
ስምምነቱ በ164 የዓለም ንግድ ድርጅት አባላት የተደረሰ ነው
የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን የባለቤትነት መብት በጊዜያዊነት ለማንሳት ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
ስምምነቱ በዓለም ንግድ ድርጅት 164 አባል ሃገራት ነው የተደረሰው፡፡
የባለቤትነት መብቱ መነሳት አለበት የለበትም በሚል ለባለፉት ሁለት ዓመታት ረዥም ክርክርን ሲያደርጉ የነበሩት የድርጅቱ አባል ሃገራት ትናንት አርብ ምሽት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም መሰረት የክትባቶቹ የባለቤትነት መብት ለጊዜው ይነሳል ተብሏል፡፡
ሆኖም የባለቤትነት የፈጠራ መብቱ መነሳት ይህን ያህል ያደጉ እና ያላደጉ ተብሎ በሚጠሩ ሃገራት መካከል ባለው የክትባት አቅርቦት የሰፋ ልዩነት ላይ የጎላ ለውጥ ላያመጣ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ኮሮና ወረርሽኝ ቢሊዬነር ያደረጋቸው 9 አዳዲስ የዓለማችን ቱጃሮች
አድገናል የሚሉ ሃገራት ክትባቶችን ማጋበሳቸውን ትተው በፍትሐዊነት ላለደጉ ሃገራት ጭምር እንዲደርስ ወረርሽኙ የከፋ አደጋን ደቅኖ በነበረባቸው በባለፉት ሁለት ዓመታት ተጠይቋል፡፡
በተለይም ደቡብ አፍሪካ እና ህንድ ስግብግብነት ነው በሚል ያደጉ ሃገራትን እርምጃ ተቃውመዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፓርታይድ ነው በሚል ድርጊቱን ኮንነው በክትባቶች ላይ ያለው የፈጠራ የባለቤትነት መብት እንዲቀር መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ሆኖም ክትባቶቹን የሚያመርቱት አደግን ባይ ሃገራት ጥያቄውን ሳይቀበሉ ቆይተዋል፡፡ ትናንት ምሽት የተሰማው ስምምነት ግን ደሃ ሃገራት ያለ ማንም ከልካይነት ክትባቶቹን ማምረት እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው፡፡
ጊዜያዊ ነው የተባለው ስምምነት ከስድስት ወራት በኋላ በድጋሚ ሊታይና ሙሉ በሙሉ ሊነሳ እንደሚችልም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
እስከተያዘው ወርሃ ሰኔ አጋማሽ ድረስ በመላው ዓለም 14 ቢሊዮን ዶዝ ክትባቶች መመረታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡