የዓለም ንግድ ድርጅት ዓለም ወደ “ዓለም አቀፋዊ ውድቀት” እየተንደረደረች ነው ሲል አስጠነቀቀ
ዋና ዳይሬክተሯ እድገትን ለማነቃቃት ስርነቀል ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል
ዋና ዳይሬክተሯ የምግብ ዋስትናን "እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል የሚለው ጉዳይ ያስጨንቀኛል” ብለዋል
የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ ዓለም ወደ “ዓለም አቀፋዊ ውድቀት” እየተንደረደረ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡
በዩክሬን ያለው የሩሲያ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ቀውስ፣ የምግብ ዋጋ እና የኢነርጂ ድንጋጤ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዘዝ ለዓለም የኢኮኖሚ ውድቀት ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ እድገትን ለማነቃቃት ስር ነቀል ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል ።
ዋና ዳይሬክተሯ በጄኔቫ እየተሳለጠ ባለው ዓለም አቀፉ የንግድ ፎረም መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር “ወደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ድቀት እየገባን ያለ ይመስለኛል፤ እናም በተመሳሳይ ጊዜ ስለ ማገገም ማሰብ መጀመር አለብን ፤እድገትን መመለስ አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የንግድ ትንበያ ቁጥሮች የሚያመላክቱት ነገሮች ጥሩ እንዳመይሆኑ ነውም ብለዋል ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ ፡፡
አክለውም “የደህንነት ፣ የአየር ንብረት፣ የኢነርጂ ፣ የምግብ ዋጋ መናር ስጋቶች አሉብን ፣ስለዚህም እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባሉበት እንደተለመደው ቢዝነስ ለመስራት አንችልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የናይጄሪያ ፋይናንስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ “ማዕከላዊ ባንኮች የወለድ ምጣኔን ከማጥበቅ እና ከመጨመር በስተቀር ብዙ ምርጫ የላቸውም - ነገር ግን በታዳጊ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ የሚያስከትሉት መዘዞች በጣም ከባድ ናቸው ምክንያቱም እነሱም የወለድ ምጣኔን ይጨምራሉ”ማለታቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል
ዋና ዳይሬክተሯ፤ ማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ግሽበት በጠንካራ ፍላጎት ወይም የዋጋ ንረቱ በአቅርቦት በኩል ካለው መዋቅራዊ ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ኦኮንጆ-ኢዌላ፤ ዋነኛ ትኩረታቸው የምግብ ዋስትናን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል እና ከዚያም የኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
“የሚያስጨንቀኝ በቂ ምግብ ካለማግኘት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው ብለዋል፡